መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ግንባሩ ለኢሳት በላከው መረጃ መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓም የግንባሩ ታጋዮች ወደ ጋይንት ከተማ በመግባት ከምሽቱ 2 ሰአት ተኩል ላይ በብአዴን ጽ/ቤት እና ሹመት በተባለው አስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ መኖሪያ ቤት ላይ ቦንብ በመወርወር ጉዳት ማድረሳቸውንና ማሽቱም በተኩስ ሲናወጥ ማደሩን ገልጿል።
ሹመት የተባለው የደህንነት አባል ከዚህ በፊት በተደረገው ህዝባዊ አመጽ ላይ የአንድ ዪንቨርስቲ 2ኛ ዓመት ተማሪ 2 ዓይኑን በጥይት ያጠፋ ከመሆኑም በላይ የአካባቢውን ህ/ሰብ “የሚገድል፡ የሚያስገድል፡ የሚያሳፍን፡ የሚያሰቃይ ” መሆኑን መረጃው አመልክቷል። በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ አጣርቶ እንደሚያቀርብም ገልጿል።
በሌላ በኩል በጎንደር ዙሪያ ደጎማ ከተማ የደህንነት አባል በሆነ ቢራራ ስመኝ በተባለ ግለሰብ ላይ መጋቢት 13 ቀን ከቀኑ 9:40 ላይ ልዩ ቦታው አይና ሽዋና በተባለ ቦታ ላይ እርምጃ እንደተወሰደበት ገልጿል። የግለሰቡ ቀብርም ደጎማ አይና ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።
በታጋዮቹ ላይ ምንም የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ድርጅቱ አስታውቋል። ጥቃቱን በተመለከተ በገዢው ፓርቲ በኩል እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።
አርበኞች ግንቦት7 ሰሞኑን ያደረሳቸውን ተከታታይ ጥቃቶች ተከትሎ፣ ታጋዮችን አውጡ፣ በሰላም እንዲገቡ አድርጉ በሚል በርካታ አርሶአደሮች እየተያዙ መደብደባቸውና መታሰራቸውን አርሶአደሮቹ ተናግረዋል።