አርበኞች ግንቦት 7 በተለያዩ አካባቢዎች የጀመረው የሽምቅ ጥቃት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

መጋቢት 13: 2009)

አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሰሞኑን በሰሜንና ደቡብ ጎንደር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የጀመረው የሽምቅ ጥቃት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ የንቅናቄው ሰራዊት አባላት በማክሰኝት፣ በደጎማ፣ በደንቀዝን ፣ በበለሳ፣ በአዲስ ወረዳ፣ በደምቢያ እንዲሁም በጯሂት በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ስርዓት ተቋማት ላይ የተቀናጀ የሽምቅ ጥቃት ማድረሳቸውን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በሰሜንና ደቡብ ጎንደር በተካሄዱ የንቅናቄው የሽምቅ ጥቃት መንግስት ቀይ ቀጠና ብሎ በሰየመው በመተማ መስመር በጭልጋ ወረዳ በቆላድባ፣ አብራጅ፣ በቸንከር ቀበሌ በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎችና የጦር ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በስርዓቱ አገልጋዮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ አብራርቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ የንቅናቄው ሰራዊት አባላት በሰሜንና ደቡብ የጎንደር አካባቢዎች ሲያካሂዳቸው የነበሩ ጥቃቶችን አስመልክቶ ንቅናቄውና ነዋሪዎች ለኢሳት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

መንግስት በበኩሉ በአካባቢው ጥቃት መፈጸሙን በማረጋገጥ በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ላይ እርምጃ መወሰኑን ሲገልፅ ቆይቷል።

በዚሁ ጥቃት ዙሪያ መግለጫን ያወጣው ንቅናቄው እርምጃው ቀጣይ እንደሚሆን አክሎ አመልክቷል።

እስካሁን በጎንደር በተደረጉ ትግሎች የታየው የህዝብ ንቁ ተሳትፎ አበራታች ነው ሲል በመግለጫው ያሰፈረው አርበኞች ግንቦት 7 መጋቢት 3 በጎንደር አጼ ፋሲለደስ ስታዲየም የተገኘው ህዝብ የአገዛዙን ዛቻ ሳይፈራ ለታጋይ አርበኛ ጎቤ መልኬ የህሊና ጸሎት ማድረጉ ለአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗል ሲል መግለጫው አመልክቷል።

ኢትዮጵያን ከህወሃት አገዛዝ ነጻ የማውጣት ሃላፊነት የወደቀው በአማራ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመላ ኢትዮጵያ ላይ ነው ያለው አርበኞች ግንቦት 7 አገዛዙን ለማስወገድ የሚደረገው ተጋድሎ ከአማራ ክልል ውጭ ወደ ሌሎች ግዛቶች እንዲስፋፋ ግንባሩ ጠንክሮ ይሰራል በማለት አክሎ አስታውቋል።