መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቂርቆስ ክፍለከተማ ወረዳ 10 ከቤት መፈናቀል ጋር በተያያዘ ወረዳው ያወጣውን ማስታወቂያ ለመገንጠልና በዱሪዬዎች የተለጠፈ ነው በሚል ሰበብ በመካድ ለማስተባበል መሞከሩን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች እስከ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓም ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ በስብሰባ ላይ የተነገራቸው መሆኑን ኢሳት ዘግቦ የነበረ ሲሆን፣ መጋቢት12 ደግሞ “መንግስት መሬቱን ለቻይናና ቱርክ ባለሃብቶች ማስረከብ ስላለበት በአስቸኳይ ቤታችሁን እንድትለቁ እናሳስባለን” የሚል ደብዳቤ ተለጥፏል። በዚህ ደብዳቤ ላይ ለግል መኖሪያ ቤት ባለቤቶች የአራት ወራት፣ ለቀበሌ ቤት ተከራዮች ደግሞ የ5 ወራት የቤት ኪራይ እንደሚከፈላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ማስታወቂያውን የተመለከቱ ነዋሪዎች ወደ ወረዳው መስተዳደር ቢሮ በመሄድ ታቃውሞአቸውን ሲገልጹ፣ መስተዳድሩ ማስታወቂያውን የለጠፉት ዱርየዎች ናቸው በማለት ማስታወቂያውን ለመገንጠል ተገዷል።
ነዋሪዎች በበኩላቸው ዱሪዬ ያላችኋቸው ሰዎች ማኅተሙን ከየት አመጡት ፣ ህዝብን እንዲህ የሚያሸብር ማስታወቂያ በተለያየ ቦታ የቀበሌውን ማኅተም በመጠቀም ሲለጠፍ የት ነበራችሁ በማለት ባለስልጣኖችን ያፋጠጡ ሲሆን፣ የወረዳው አመራር አባላት ግን መልስ መስጠት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ዜጎች የመስተዳድሩን መልስ በጥርጣሬ እንደሚያዩት የተናገሩ ሲሆን፣ በማንኛውም ጊዜ ዶዘር ይዞ መጥቶ ሊጠርጋቸው እንደሚችል ወይም በሌሎች አካባቢዎች እንደሚያደርገው አካባቢውን በእሳት አቃጥሎ ከቦታቸው ሊያስነሳቸው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ከእኛ በላይ የቻይናና የቱርክ ዜጎች ተመራጭ የሆኑበት ዘመን ላይ ደርሰናል ሲሉም በምሬት ተናግረዋል።
ከ50 አመታት በላይ የኖሩበትን አካባቢ ያለ ምንም ተለዋጭ ቦታና በቂ ካሳ ልቀቁ መባላቸውን በመቃወም፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ችግራቸውን ሰምተው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡዋቸው ነዋሪዎች ተማጽነዋል።