በቴኔሲ ናሽቪል ከተማ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሆቴልን የገደለ ተጠርጣሪ ለመያዝ ፍለጋው ተጠናክሮ ቀጥሏል

ኢሳት (መጋቢት 12: 2009)

የአሜሪካ ፖሊሶች በሳምንቱ መገባደጃ ዕሁድ በዚህ በአሜሪካ የቴኔሲ ግዛት ናሽቪል ከተማ ኢትዮጵያዊ ባለሆቴሉን የገደለ ተጠርጣሪን ለመያዝ ለሶስተኛ ቀን ፍለጋ አጠናክረው መቀጠላቸውን ገለጡ።

የ41 አመቱ ኢትዮጵያዊ አቶ ግጠም ደምሴ  አይቤክስ የተባለውን የምግብ ቤቱን ቅዳሜ ምሽት ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ድርጅቱን ዘግቶ በመውጣት ላይ እንዳለ ፊቱን የሸፈነ ግለሰብ በተደጋጋሚ የተኩስ ዕርምጃን በመውሰድ ግድያ መፈጸሙን የግዛቲቱ ፖሊስ አስታውቋል።

የናሽቢል ፖሊስ በከተማዋ ከ10 አመት በላይ የኖረውን ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል ከእማኞች የተገኘን መረጃ መሰረት በማድረግ ፍለጋውን አጠናክሮ እንደቀጠለ የግዛቲቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኒውስ ቻናል 15) ዘግቧል። ተጠርጣሪው ጭንብል ያጠለቀ ግለሰብ መሆኑም ከቤቱና ከአካባቢው ካሜራዎች የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ከእማኞችና ከካሜራ የተገኙ አካላዊ ምልክቶችን መሰረት በማድረግ ፍለጋውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል። የወንጀሉን ምክንያት መነሻ ለማወቅም የቴኔሲ ግዛት ናሽቢል ልዩ የመርማሪ አካላት ተመሳሳይ ምርመራ እያካሄዱ እንደሆነም ታውቋል።