ኢሳት (መጋቢት 12: 2009)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ላለው የድርቅ አደጋ የሚያስፈልገው አለም አቀፍ ድጋፍ እየተገኘ ባለመሆኑ ድርቁ እያደረሰ ያለው አደጋ እየተባባሰና ስጋት እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ።
ይኸው የድርቅ አደጋ በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በርካታ ሰዎች በከፋ የምግብ እጥረት የአካልና የጤና ችግር እንዲደርስባቸው ያደረገ ሲሆን፣ ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆነ ህጻናት ወደ ማገገሚያ ማዕከል እየገቡ መሆኑን ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ በሚያወጣው ሳምንታዊ ሪፖርት አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ያጋለጠውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ከወራት በፊት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና ድጋፉን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብም በቂ ምላሽ አለመገኘቱን እና የድርቁ አደጋ እየተባባሰ መምጣቱ ተመልክቷል።
በሶማሌ ክልል አፍዴር አካባቢ ብቻ ወደ ማገገሚያ ማዕከላት የሚገቡ ህጻናት ቁጥር በ65 በመቶ መጨመርን ያሳየ ሲሆን፣ ከስድስት ሺ በላይ ህጻናት በማዕከሉ እንደሚገኙ ታውቋል።
በጃራር እና በዶሎ አካባቢዎች ወደ ማገገሚያ ጣቢያ እየገቡ ያሉ ህጻናት ቁጥር በ600 እና በ300 ፐርሰንት ማሻቀቡንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊገኝ የታሰበው የገንዘብ ድጋፍ በወቅቱ ባለመገኘቱ ምክንያት የሰብዓዊ ዕርዳታን ለመስጠት የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለችግሩ መድረስ ሳይችሉ መቅረታቸውም ተገልጿል።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ከወራት በፊት በተከሰተው የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ መጋለጣቸው ይታወሳል።
አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ በቂ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ባለማግኘቱ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። መንግስት በበኩሉ ድርቁ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።