በአንድ ኢትዮጵያዊ የእስራዔል ወታደር ላይ ድብደባን የፈጸመ ፖሊስ በወንጀል ሊከሰስ እንደሚችል ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 12: 2009)

የእስራዔል የፍትህ ሚኒስቴር ከሁለት አመት በፊት በአንድ ኢትዮጵያዊ የእስራዔል ወታደር ላይ ድብደባን የፈጸሙ ፖሊስ በወንጀል ሊከሰስ እንደሚችል አስታወቀ።

ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው የቀድሞ አቃቤ ህግ ተጀምሮ ፍርድ ሳያገኝ በእንጥልጥል የቆየው ድርጊት እንዲዘጋ ባለፈው ጥር ወር ውሳኔን ቢያስተላልፍም ጉዳዩ ይግባኝ ቀርቦበት በአዲስ መልክ መታየት መጀመሩን የእስራዔል መገናኛ ተቋማት የእስራዔልን የፍትህ ሚኒስቴር ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል።

የፖሊስ ባልደርባው የቀረበለትን ወንጀል የማያምንና ቅጣት ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ የተቋረጠው ክስ እንዲቀጥል እንደሚያደርግ የእስራዔል የፍትህ ሚኒስቴር አዲስ አማራጭ ማቅረቡን ታይምስ ኦፍ እስራዔል የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

የፖሊስ ባልደርባው የደንብ ልብስ ለብሶ በነበረው ኢትዮጵያዊ የእስራዔል ወታደር ላይ የፈጸመው ድብደባ በቪዲዮ ለህዝብ ከተሰራጨ በኋላ በሃገሪቱ በሚኖሩ ቤተ እስራዔላዊያንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።

ደማስ ፒካዳ ላይ ድብደባውን የፈጸመው የእስራዔል ፖሊስ ከስራው እንዲሰናበት ቢደረግም በፈጸመው ድርጊት ክስ ሳይመሰረት መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና በፖሊሱ ላይ የወንጀል ክስ ባለመመስረቱ ኢትዮጵያዊው የእስራዔል ወታደር እንዲሁም የሰብብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት አቤቱታን እንደሚያቀርቡ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይህንኑ ቅሬታ ተከትሎም የእስራዔል የፍትህ ሚኒስቴር ድብደባውን የፈጸመው ፖሊስ የቀረበበትን ወንጀል አምኖ ቅጣት ለመቀበል ፈቃደኛ እንዲሆን ካልሆነም የወንጀል ክስ እንዲመሰረትበት ወስኗል።

የፍትህ ሚኒስቴሩ የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ መሆኑን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ገልጸዋል።

የእስራዔል ፖሊስ ባልደርባውን ከስራ ካሰናበተ በኋላ ክስ መመስረት የሚያስችል ምክንያት የለም ሲል ውሳኔን ሰጥቶ እንደነበርም ታይም ኦፍ እስራዔል አውስቷል።

ይህንኑ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱ የህግ አካላት የጠቡ መነሻ ወታደሩ ነው በማለት ውሳኔን ቢያስተለፉም ድርጊቱ አዲስ ቅሬታን ቀስቅሶ ቆይቷል።

የእስራዔል የፍትህ ሚኒስቴር ለሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አማራጭ ያለውን ሃሳብ ቢያቀርብም ፖሊስ ጥፋቱን ካመነ ምን አይነት ቅጣት እንደሚተተላለፍበት የሰጠው መረጃ የለም።

ሚኒስትሩ ያቀረበውን ይህንኑ አማራጭ ተከትሎም የእስራዔል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ዳግም መመልከት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በድርጊቱ በተለያዩ የእስራዔል ከተሞች ተቀስቅሶ የነበረውን ተቃውሞ ለማብረድ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸው ይታወሳል።