ከሳውድ አረቢያ ይገኛል የተባለው ገንዘብ በመቅረቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ተባብሷል

መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአስመጪነት የተሰማሩ ባለሃብቶች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ስራ መስራት በማይችሉበት ደረጃ ላይ ቢደርሱም እንዲሁም በርካታ ፋብሪካዎችም የመለዋወጫ እቃዎችን ማስመጣት እየተሳናቸው ሰራተኞችን መቀነስ ቢጀመሩም፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ከሳውድ አረቢያ የሚገኘው ብድር እስካሁን ሊገኝ ባለመቻሉ፣ እጥረቱ ተባብሶ ቀጥሎአል።
የሳውዲ መንግስት በአጭር ጊዜ ብድር እስከ 1 ቢሊዮር ዶላር እንደሚያቀርብ ተስፋ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ገንዘቡ እስካሁን አለመቀቁ ታውቋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በአንድ ወቅት ገንዘቡ ወደ አገሪቱ ሲገባ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ እንደሚቀረፍ ተስፋ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በሳውዲ በኩል የሚጠበቀው ገንዘብ ባለመምጣቱ ችግሩ እየተባባሰ ነው። ከሳውዲ በኩል የሚጠበቀው ገንዘብ ለምን እንዳልተለቀቀ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
በኦሮምያ፣ ደቡብና አማራ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ የውጭ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶአል።ከወጪ ገበያ ይገኛል ተብሎ የታቀደው የውጭ ምንዛሬ ከግማሽ ባላነሰ መጠን ቀንሷል። ዲያስፖራው ወደ አገሩ የሚልከው ገንዘብ እያነሰ መምጣቱ እንዲሁም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሰጠው የውጭ እርዳታ መቀነሱ፣ በአገሪቱ ለተፈጠረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያቶች ተደርገው ይቀርባሉ። ከህዝባዊ አመጹ በሁዋላ ወደ ውጪ በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብም እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። የቱሪዝም መዳከም እንዲሁም በፊት በተከታታይ ይደረጉ የነበሩ አለማቀፍ ስብሰባዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሁዋላ በመቀነሳቸው ለውጭ ምንዛሬ እጥረቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
አገሪቱ ቀደም ብሎ ለተበደረቻቸው ብድሮች የምትከፍለው ወለድ እየጨመረ መምጣቱ፣ በአገሪቱ ከተንሰራፋው ሙስና እና የንብረት ብክነት ጋር ተደማምሮ ችግሩን አባብሶታል።
በአሁኑ ሰአት የንግድ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክመው የሚገኙ ሲሆን ፣ በመንግስት የሚደረጉ ግንባታዎች ሳይቀሩ እየቆሙ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የኢኮኖሚ ችግር መቀጠል፣ በዜጎች ህልውና ላይ ከባድ ፈተና መደቀኑን ዘጋቢያችን የላከው ሪፖርት ያመለክታል።