መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ ሊቀመንበር አቶ ዓለማየሁ መኮንን፣ የዞኑ ጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ አጠቃላይ 11 አባላት ከመኖሪያ ቤታቸው ታግተው ከተያዙበት ሕዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከአራት ወራት በላይ በእስር ሲሰቃዩ ቆይተው መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በዋስ ተፈተዋል።
በእስር ቤት ውስጥ ምንም ዓይነት ምግብ እንደማይቀርብላቸውና ለብቻቸው እንዲታሰሩ ተደርገዋል። የድርጅታቸው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ ዳዊት ታመነ ለብቻው በጨለማ እየተጠራ ማስፈራራት የደረሰበት ሲሆን እስካሁን ማን እንዳሰራቸው ማወቅ እንዳልቻሉም አስታውቀዋል።
በመኖሪያ ቤታቸው እና ጽ/ቤቶቻቸው ፍተሻ በማድረግ ንብረቶቻቸው መወሰዱነና ከሕግ አግባብ ውጪ መኖሪያ ቤታቸው፣ኮምፒተራቸው መበርበሩን፣ ድምጽማጉያዎች፣ ሞባይሎች፣ የተለያዩ ማስታወሻዎች፣ መጽሃፍትን እና የተለያዩ ንብረቶቻቸው ተወስዶባቸዋል። አስቸኳይ አዋጁ ከመታወጁ በፊት ለተለያዩ መገናኛ ቡዙሃን የሰጡትን ቃለመጠይቆች በመረጃነት በማቅረብ በአቃቤ ሕግ አስቸኳይ አዋጁን በመጥቀስ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በኮማንድ ፖስቱ ከሰላማዊ ታጋዮች ከኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ አመራሮችና አባላት በተጨማሪ የዞኑ የሙስሊም ወኪሎች ለእስር ተዳርገው ነበር። የደቡብ ኦሞ ዞን የሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አብዱል መሊክ፣ አቶ ዱባለ ደምሴ የዞኑ እስልምና ጉዳይ ሃላፊ፣ አቶ ናስር ዓሊ የዞኑ እስልምና ሰብሳቢ ታስረው ከቆዩ በዋስ ተፈተዋል።