መጋቢት ፲፩ (አሥራ አንድ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ብአዴን ሚስጢሮቹ የሚባክኑት እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ ያለው አለመተማመን እንዲጨምር ያደረገው ከፍተኛ አመራሩ በድርጀቱ ላይ እምነት እያጣ በመምጣቱ ነው ሲሉ የብአዴንና የህወሃት ባለስልጣናት ተናግረዋል። ብአዴን ቅዳሜ ባካሄደው ስብሰባ ፣ ከብአዴን መሪዎች አቶ አለምነው መኮንን፣ ከህወሃት ደግሞ አቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስ በስልክ የተሳተፉ ሲሆን፣ ህወሃት የብአዴን ከፍተኛው አመራር እንዲሁም የክልሉ ሚዲያ እና ጋዜጠኞች ጸረ ህወሃት አቋም እንደሚያንጸባርቁ ሃሳብ አቅርቧል። ብአዴን ጋዜጠኞች በመድረክ ላይ ያቀረቡት ሀሳብ የራሳቸው እንጅ ከፖለቲካ ስርዓቱ ጋር ምንም ግንኙት የለውም በማለት ተከራክሯል።
ከብአዴን አመራር በኩል ለኢሳት የሚደርሰው መረጃ መፍትሄ ካልተበጀለት፣ ከፍተኛ አመራሩ ከኦህዴድ በባሰ ለኢህአዴግ ህልውና አደጋ እንደሚፈጥር የህወሃት ተወካዮች ገልጸዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ብአዴን ከአሁን በሁዋላ በእሱ በኩል የሚወጡ መረጃዎችን መድፈን ፣ ቀዳሚ አጀንዳዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ውጭ እንዳያውቁና ተሳታፊዎችንም አስቀድሞ የመለየት ስራ በመስራት እንዲቆጣጠሩ ስብሰባው ውሳኔ አሳልፏል።
በተለያዩ የክልሉ ባለስልጣናት እና ጋዜጠኞች ላይ በድብቅ ክትትል የሚያደርጉ ሰዎች የተመደቡ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት የክልሉ ባለስልጣናት እና ጋዜጠኞች ሳይቀር እርስ በርስ ተፈራርተው እንደሚገኙ ታውቋል።
የብአዴን ነባርና ዋናዎቹ መሪዎች በይደር የያዙዋቸውን አጀንዳዎች ሳይወያዩባቸው ቀርተዋል። የመረጃ መውጣትን ለመከላከል በሚመስል በኩል ዋና ዋና ሹሞች ወደ አዲስ አበባ አምርተዋል።