ኢሳት ( መጋቢት 7 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በደረሰ የቆሻሻ መደርመስ አደጋ የሟቾች ቁጥር ወደ 200 አካባቢ ሊደርስ እንደሚችል ነዋሪዎች አስታወቁ።
ለአምስተኛ ቀን በተካሄደ ቁፋሮ የሟቾች ቁጥር 115 የደርሰ ሲሆን፣ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች በበኩላቸው 80 ነዋሪዎች አሁንም ድረስ የገቡበት አለመታወቁን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል። አስከሬን የማፈላለግ ስፍራው ተጓትቷል ሲሉ ቅሬታቸውን ሲገልጹ የቆዩ ነዋሪዎች መንግስት ቸልተኝነት አሳይቷል ሲሉ ቅሬታን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቃል አቀባይ ዳግማዊት ሞገስ ረቡዕ ምሽት ድረስ የሟቾች ቁጥር ከ82 ወደ 115 መድረሱንና ቁፋሮውም ሃሙስ መቀጠሉን ለሮይተርስ አስረድተዋል።
አቶ ተመስገን አብራሃም የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው ከቆሻሻ ክምሩ አሁንም ድረስ ያልወጡ ወደ 80 አካባቢ ሰዎች መኖራቸውን ለዜና አውታሩ አስታውቀዋል።
ቁፋሮች በአግባቡ ተጠናክሮ ቢቀጥል ተጨማሪ አስከሬን በአፋጣን ሊገኝ እንደሚችል አቶ ተመስገን ገልጸዋል።
ቅዳሜ ምሽት የቆሻሻ ክምሩ አደጋ በደረሰ ጊዜ 48 አካባቢ ቤቶች መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ መኖሪያ ቤት በአማካኝ ሰባት ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ታውቋል።
የከተማው አስተዳደር የወደሙ ቤቶችን ቁጥር ቢያረጋግጥም አደጋው በደረሰ ጊዜ ምን ያህል ሰው በቦታው እንደነበር አለመታወቁን አመልክቷል። ከአደጋው የተረፉ ነዋሪዎች ቁፋሮው በአፋጣኝ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የጠፉ ሰዎች አስከሬን ፍለጋው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው አስከሬን የማፈላለጉ ስራ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ይሁንና የቤተሰብ አባሎቻቸውን ሁኔታ ማወቅ ያልቻሉ ከአደጋው የተረፉ ነዋሪዎች የሁሉም አስከሬን እስኪገኝ ድረስ ቁፋሮው እንዲቀጥልና በቂ ቁሳቁስ እንዲሰማራ ጠይቀዋል። እስከ ረቡዕ ድረስ ህይወታቸው ማለፉ ከተረጋገጠው 115 ሟቾች መካከል 75ቱ ሴቶች ሲሆን፣ 38 ወንዶች መሆናቸው ታውቋል። ከ15 የሚበልጡት ህጻናት ናቸው።
የቁፋሮው ስራው ተስተጓጉሏል በማለት ቅሬታን ሲያቀርቡ የነበሩ ነዋሪዎች በግላቸው ገንዘብ እየከፈሉ የቤተሰብ አባሎቻቸውን አስከሬን ሲያፈላልጉ እንደነበር ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል።
በስፍራው ተጨማሪ አደጋ ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ አንድ ወጣት ማዕከል እንዲጠለሉ የተደረገ ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እንዲያደርግ አስታውቋል።
በማዕከሉ ተጠልለው ለሚገኙ ሰዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በየዕለቱ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሆነም ታውቋል። አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እንዲሁም ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ለአሳዛኙ ድርጊት መድረስ መንግስትን ተጠያቂ አድርገዋል።
ይሁንና የመንግስት ቃል አቀባይ ነገሪ ሌንጮ የአካባቢው ነዋሪዎች በቆሻሻ ክምሩ ላይ ቁፋሮን በማካሄዳቸው አደጋው ሊደርስ መቻሉን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደር በስፍራው ለባዮ-ፊዩል የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ዝግጅት ሲካሄድ የቆየው የመሬት መደልደልና ስራ በቆሻሻ ክምሩ ላይ ጫና ማሳደሩን ለአደጋው መንስዔ መሆኑን ሲገልፅ ቆይተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት በአካባቢው ነዋሪዎች ህይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ሲኖሩ በዝምታ ተመልክቷል። እንዲሁም በስፍራው ከመጠን በላይ ቆሻሻ እንዲጣል አድርጓል በማለት መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል።
በተያያዘ ዜናም መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎችና የአለም አቀፉ ተቋማት በአደጋው የተሰማቸውን ሃዘን በመግለፅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሜሪካና የጀርመን ኤምባሲዎች ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው አደጋ እጅጉን ማዘናቸውን አስታውቀው በየኤምባሲያቸው ቅጥር ግቢ የየሃገራቱ ኤምባሲ ሰንደቅ አላማ በግማሽ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ መወሰናቸውን ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት አመልክተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኤኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) እንዲሁም ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ተመሳሳይ የሃዘን መግለጫን አውጥተዋል።