የአዲስ አበባ መስተዳድር ሰራተኞች በቆሼ ለደረሰው አደጋ መስተዳድሩን ተጠያቂ አደረጉ

መጋቢት ፯ (ሰባት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ ከተማ ቆሼ ተብሎ በሚታወቀው የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በመሙላቱ ምክንያት፣ ቆሻሻ መጣያ ስፍራውን በመዝጋት ወደ ታሪካዊ መናፈሻነት ለመቀየር እየሰራ መሆኑንና ሥራውም ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ከአራት ዓመት በፊት በወቅቱ ከንቲባ በነበሩት በኩማ ደመቅሳ ሪፖርት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት አራት ዓመታት ግን ቆሻሻ መድፊያውን በተግባር መዝጋት ባለመቻሉ የአሁኑ አደጋ መከሰቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአስተዳደሩ ባለሙያዎች መረጃ ጠቅሰው ተናግረዋል።
«የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የአምስት ዓመት (ከ2001-2005) ዋና ዋና የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች» በሚል ርእስ በሰኔ ወር 2005 ዓ.ም ለአስተዳደሩ ም/ቤት በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በቀረበው ሪፖርት መሰረት ቆሸ ቀደም ብሎ መዘጋት ነበረበት። በጊዜው መስተዳድሩ ባቀረበው ሪፖርት ላይ «…ለ47 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውንና በተለምዶ ቆሼ በመባል የሚታወቀውን 19 ሄክታር የረጺ ቆሻሻ መድፊያ ቦታን በመዝጋት በጥናት ላይ በተመሰረተ አኳሃን ደረጃውን የጠበቀ ታሪካዊ የመናፈሻ ሥራ ተጀምሮአል፡፡ አፈጻጸሙም ከ80 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡” ሲል ገልጾ ነበር።
መስተዳድሩ “ ከዚሁ ጎን ለጎን አዲስ ሳኒተሪ ላንድፊል ግንባታ ለማካሄድ በከተማዋ ሰሜን ምስራቅ ለገጣፎ በሚገኘው ክልል ስፋት ያለው ቦታ ተመርጦ የአጥርና የዲዛይን ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አራት የቅብብሎሽ ጣቢያዎች ግንባታና የደረቅ ቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች የዲዛይን ጥናት ስራ እየተሰራ ይገኛል» ሲል ያክላል።
የቆሻሻ መድፊያ ቦታው መሙላቱ ከታወቀ በሁዋላ እንደሚዘጋ ተገልጾ በወቅቱ ባለመዘጋቱ የሰሞኑ አደጋ ሊከሰት እንደቻለ የመስተዳድሩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በለገጣፎ አካባቢ ቆሻሻ የመጣል ስራ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ከኦሮሚያ ሕዝባዊ አመጽ ጋር ተያይዞ የአካባቢው ሕዝብ «እኛ ቆሻሻ መጣያ አይደለንም» የሚል ተቃውሞ በማስነሳቱ እንዲሁም የአስተዳደሩም ሆነ የግል ቆሻሻ አንሺ ተሽከርካሪዎች በርቀቱ ምክንያት በፍጥነት ተመላልሰው የከተማዋን ቆሻሻ ማንሳት ባለመቻላቸው ከተማው የባሰውኑ እንዲቆሽሽ ምክንያት ሆኖ ታይቶአል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አስተዳደሩ ሌላ ተለዋጭ ቆሻሻ መጣያ ቦታ መፈለግ ሲገባው፣ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ «ሞልቶአል» ባለው ቆሼ አካባቢ እንደገና ቆሻሻ መጣል በመቀጠሉ አሁን ለተፈጠረው አደጋ ዋንኛ መንስኤ መሆኑን ሰራተኞች ይገልጻሉ።
አስተዳደሩ በሕዝብ ላይ ለደረሰው አሰቃቂ ጉዳት በገለልተኛ ወገን ተጠያቂዎች መሆን አለባቸው ሲሉ የመስተዳድሩ ሰራተኞች ገልጸዋል።
አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፣ በህዝብ ላይ ለደረሰው እልቂት የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ ተጠያቂ አድርጓል።
እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ ከ113 ሰዎች በላይ አስከሬን የተገኘ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን አሁንም በርካታ ሰዎች ከተቀበሩበት አፈር አልወጡም ይላሉ።