በሴት ልጁ ላይ ግርዛት ፈጽሟል የተባለ ኢትዮጵያዊ ከ10 አመት የእስር ቅጣት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተደረገ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2009)

ነዋሪነቱ በዚሁ በአሜሪካ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ በሴት ልጁ ላይ ፈጽሞታል በተባለ ግርዛት ከ10 አመት የእስር ቅጣት በኋላ ሰኞ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተደረገ።

ነዋሪነቱ በጆርጂያ ግዛት የነበረው የ41 አመቱ ካሊድ አህመድ ከ10 አመት በፊት በሁለት አመት ህጻን ልጁ ላይ የፈጸመው ግርዛት በአሜሪካ ታሪክ የተከለከለና ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ እንደነበር ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የፍርድ ቤት ውሳኔን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። ግለሰቡ በህጻን ልዩ ፈቃድ ላይ ፈጽሞታል የተባለው ግርዛት ለ10 አመታት ያህል በህግ አካላት ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱም ታውቋል።

ግለሰቡ በሁለት አመት ህጻን ልጁ ላይ ፈጽሞት የነበረው ይኸው ድርጊት በታዳጊዋ ቀሪ ህይወት የእድሜ-ልክ ሰቀቀን አሳድሮ መቅረቱን ሻን ጋላገር የተባሉ የኢሚግሬሽንና የጉምሩክ የፊልድ ዳይሬክተር ገልጸዋል።

የሴት ልጅ ተፈጥሯዊ አካልን በግርዛት ማጉደል ዘርፉ ብዙ የጤና እክልና እንደሚያከትል ሃላፊው አክለው ተናግረዋል።

የሴት ልጅ ግርዛት በአሜሪካ በፌዴራል ደረጃ እገዳ የተጣለበት ድርጊት ቢሆንም፣ ግማሽ ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጉ ሴቶች ድርጊት እንደተፈጸመባቸው አሊያም ተጋላጭ ሳይሆኑ መቅረቱን ከአምስት አመት በአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል የተካሄደ ብሄራዊ ጥናት አመልክቷል።

ይኸው ድርጊት በተለይ በአሜሪካ በስደት በሚኖሩ የአፍሪካውያን ማህበረሰብ ዘንድ በብዛት የሚካሄድ ድርጊት በመሆኑ የአሜሪካ የህግ አካላት ልጆቻቸውን ለዕረፍት ወደ ሃገራቸው ይዘው በመሄድ ግርዛቱን እንዲያከናውን የሚከላከል ደንብ ተግባራዊ ማድረጉንም ለመረዳት ተችሏል።

የደንቡ ተግባራዊነት ተከትሎ ባለፉት 13 አመታት በድርጊቱ የተጠረጠሩ 785 ሰዎች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፣ 380 የሚሆኑ ደግሞ ለእስር መዳረጋቸውን የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ለጋዜጣው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ድርጊቱ በስፋት በሚከናወንባቸው ሶማሊያ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋልና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቀር የሃገሪቱ መንግስታት አስርተ-አመታት የቆየ ዘመቻ ሲያካሄዱ መቆየታቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) አስታውቋል።

ባለፈው አመት የሶማሊያ መንግስት የሴት ልጅ ግርዛት በህግ እንዲታገድ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ለድርጊቱ ሰለባ የሚሆኑ ሴቶች ቁጥር እየቀነሰ በመሄድ ላይ መሆኑም ይገልጻል።