መጋቢት ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ግምታቸው ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ 21 የአውራሪስ ቀንድ በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደ ታይላንድ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የታይላንድ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ባለፈው ዓርብ መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ወደ ታይላንድ ከገባ አውሮፕላን ውስጥ ክብደታቸው 50 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ በቦርሳዎች የተጫኑ ከተለመዱት የአውራሪስ ቀንዶች ለየት ያሉ እና ትላልቆች የአውራሪስ ቀንዶችን በታይላንድ አየር ማረፊያ መያዛቸውን የአገሪቱ ጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች ገልፀዋል። የቦርሳዎቹ ባለቤቶች በተለያዩ በረራዎች ተነጣጥለው የገቡ ሁለት ሴት ታይላንዳዊያን ሲሆኑ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው ቀጥሏል።
ግምታቸው ከ600 ሽህ ዶላር በላይ የሚያወጡ የአውራሪስ ቀንዶች ከዚህ በፊት መያዛቸውንና ”በዚህ አየር ማረፊያ ውስጥ ከዚህ በፊት ከያዝናቸው የአውራሪስ ቀንዶች እጅግ ውብ እና የሚያማምሩ ናቸው”ሲሉ የጉምሩክ ባለስልጣኑ አክለው ተናግረዋል።
በኤሲያ በተለምዶ የአውራሪስ ቀንዶች፣ ደም፣ ቆዳ እና ሽንት ለባሕላዊ የቻይና ሕክምና አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊ ናቸው። በተጨማሪም የአውራሪስ ቀንዶች ለቅንጦት እቃዎች መስሪያነት በተለይ በቪየትናም ተፈላጊነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን የዱር እንስሳት ተቆጣጣሪ ድርጅት አስታውቋል።
”እነዚህ የአውራሪስ ቀንዶች በጣም ትላልቅ ናቸው። ይህም ማለት ትላልቅ አውራሪሶች ተገለው የተገኙ ናቸው።” ሲሉ የአካባቢ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሚኒስቴር ዳይሬክተር ስጋታቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፓርኮች ውጭ የሚኖሩ አውራሪሶች ላይ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑንና ዝርያቸውም በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ምክንያት እየተመናመነ መምጣቱን የዓለም የዱር እንስሳት ጥበቃ ድርጅትን ጠቅሶ አሾሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።