ህዳር 26 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በስርቆት፣ በሙስናና በተለያዩ ህገወጥ መንገዶች ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር የወጣው ገንዘብ 11 ቢሊዮን መድረሱን አንድ ታዋቂ አለማቀፍ ተቋም አጋለጠ፣ ኢትዮጵያውያን እየደሙ ነው ሲል የድርጊቱን አስከፊነትም ገልጧል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሀግብር ወይም ዩኤን ዲ ፒ የገንዘብ ድጋፍ ጥናቱን ያካሄደው “ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ” የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባወጣው የቅድመ ዳሰሳ ሪፖርት ፣ እጅግ ደሀ ከሆነችው ኢትዮጵያ በአለፉት 9 አመታት ብቻ 11 ቢሊዮን ዶላር ወይም 187 ቢሊዮን ብር ተዘርፎ በውጭ አገር ባሉ ባንኮች ተቀምጧል።
የእያንዳንዱ ዜጋ አማካኝ የነፍስ ወከፍ ገቢ 365 ዶላር ብቻ በሆነባት ኢትዮጵያ፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2009 ወይም በ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 2002 ዓም ብቻ ከአገሪቱ የወጣው ገንዘብ 3.26 ቢሊዮን ዶላር ወይም 55 ቢሊዮን ብር ነው።
“እጅግ የሚያስጨንቀው ነገር ህገወጥ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ በዝርፊያ ወደ ውጭ የሚወጣው ገንዘብ እጨመረ መሄዱ ነው” የሚለው ተቋሙ፣ “ገንዘብ በህገወጥ መንገድ እየወጣ ያለው ደግሞ በዋነኝነት በየጊዜው እየጨመረ በሚሄደው ሙስና፣ ጉቦ እና ኮንትራቶችን ለማሸነፍ ለባለስልጣናት በሚሰጠው ጥቅማጥቅም ነው።”
በአለም ላይ እጅግ ደሀ ከሚባሉት አገሮች ተርታ የምትሰለፈው ኢትዮጵያ፣ በረሀብ፣ በፖለቲካ ጭቆና እና በድህነት ትታወቃለች።
በፈረንጆች አቆጣጠር በ2008 ወይም በ2001 ዓም አገሪቱ ከውጭ እርዳታ 829 ሚሊዮን ዶላር ወይም 14 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ብታገኝም፣ የውጭ እርዳታው በሙሉ እንዲሁም 40 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ በዚያኑ አመት ከአገሪቱ ለቅቆ በውጭ ባንኮች ተቀምጧል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ በዝርፊያ የተነሳ ደሙ ሁሉ ተመጥቶ አልቋል፣ የሚለው ተቋሙ፣ “ኢትዮጵያኖች ከድህነት ለመውጣት የቱንም ያክል ቢፍጨረጨሩ፣ አሁን በሚታዬው ዝርፊያ ወደ ታች የሚፈስን ወንዝ፣ ወደ ላይ በመዋኘት ለመጨረስ ሙከራ እንደማድረግ ይቆጠራል።” ሲል የመለስ መንግስት ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ አሰልፋታለሁ እያለ በየጊዜው የሚያውራውን ወሬ ተረት ተረት አድርጎታል።
የአለማቀፉ የገንዘብ ስርአት በስርቆት የተገኘውን ገንዘብ ለማስተናገድ አመቺ መሆኑንም ተቋሙ ገልጧል።
የኢትዮጵያን ህዝብ እያደሙ የሚገኙት ዘራፊዎች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል በሙስና የተጨማለቁት የመንግስት ባለስልጣናት እና ታክስ የሚያጭበረብሩ አለማቀፍና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ይገኙበታል።
ድርጅቱ እንዳለው የአለማቀፍ መንግስታት ገንዘብ በህገወጥ መንገድ የሚያዙዋዙሩትን የመንግስት ባለስልጣናትና ሸሪኮቻቸውን እንዲሁም እንዲህ አይነቱን ተግባር የሚፈጽሙትን ኩባንያዎች መቆጣጠር አለበት። ከኢትዮጵያ ደሀ ህዝብ የሚዘረፈውን ገንዘብ በማስቆም ህልቆ መሳፍርት የሆነ ህይወት ማዳን እንደሚቻል ተቋሙ ጠቅሷል።
አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በቅርቡ ባወጡት ጥናታዊ ጽሁፍ ከኢትዮጵያ የተዘረፈው 8 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት ቢመለስ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ የሚዋጣውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሸፍኖ፣ 90 የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፤ 18 ዩኒቨርሲቲዎች ፣ 27 ኮሌጆች ፤ 36 ዘመናዊ ሆስፒታሎች ፤ 180 ጤና ጣቢያዎች ፤ 6 የዘይት ፋብሪካዎች ፤ 4 የስሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሁም አራት እጂግ ከፍተኛ የሚባሉ አግሮ ኢንደስትሪዎችን ለማቋቋም ያስችላል።
አሁን ይፋ የሆነው አሀዝ ሁለት የአባይ ግድቦችን፣ 90 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንና 18 ዩኒቨርስቲዎችን ለመገንባት እንደሚያስችል መረጃዎች ያመልክታሉ።
በጥናቱ በገንዘብ ዝርፊያው የተሰማሩት ባለስልጣናት ስም ባይገለጥም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሙስናዎች እናት ተብለው የሚታወቁት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የዝርፊያው ቁንጮ ሊሆኑ እንደሚችል አንድ ስማቸውን መግለጥ ያልፈለጉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ይናገራሉ።
ይህ ዜና በልመና ለቆመው የመለስ መንግስት አስደንጋጭ ይሆናል ሲሉ ኢኮኖሚስቱ ያክላሉ።
አቶ መለስ የሚለምኑት ገንዘብ የእርሳቸውን እና የባለስልጣኖቻቸውን የግል ካዝና ለመሙላት ነው በማለት ኢትዮጵያውያን ምሁራን ሲያቀርቡት የነበረው ትችት በአለማቀፍ ተቋማትም እየተደገፈ መምጣቱንም ባለሙያው አክለው ተናግረዋል።
በትራንስፎርሜሽን እና እድገት ስም የመለስ መንግስት ባለፉት 10 አመታት ብቻ ከቻይናና ከህንድ መንግስታት ከ 25 ቢሊዮን ዶላር በላይ መበደሩን መዘገባችን ይታወሳል።
የመለስ ባለስልጣናት ለሚያካሂዱት ዘረፋ ፣ መጪው ትውልድ ከፍሎ የማይጨርሰው እዳ ውስጥ እየገባ ነው።