ኦህዴድ ከሶማሊ ድንበር ጋር በሚዋሰኑ ወረዳዎች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የሶማሊ ክልልን ተጠያቂ አደረገ

መጋቢት ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦሮምያ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በጻፉት ጽሁፍ በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ስር ባሉ ቁምቢ፣ጭናክሰን፣ ሚደጋ ቶላ፣ጉርሱም፣መዩ ሙሉቄ እና ባቢሌ ወረዳዎች፤ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የሚገኘዉ የጉምቢ ቦርዶዴ ወረዳ፣ በባሌ ዞን የሚገኙት ዳዌ ሰረር፣ሰዌና፣ መደ ወላቡ እና ራይቱ ወረዳዎች፣በጉጂ ዞን ጉሚ ኢደሎና ሊበን ወረዳዎች በቦረና ዞን የሚገኘዉ ሞያሌ ወረዳ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አውስተው፣ ጥቃቱንም በሶማሊ ክልል ታጣቂዎች መፈጸሙን ይገልጻሉ።
አቶ አዲሱ በጽሁፋቸው በሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢ ለተነሳውና በርካታ ዜጎች ለተገደሉበት ግጭት ከኦሮምያ የሚነሱ የታጠቁ ሃይሎች መነሻ እንዲሆነ ተደርጎ የሚቀርበውን ክስ አጣጥለዋል። ቀደም ብሎ በ1997 ዓም በሁለቱ ክልሎች መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ አወዛጋቢ ከሆኑት ከ420 ቀበሌዎች ውስጥ ሰማንያው ወደ ሶማሊ ክልል እንዲገቡ ቢወሰንም፣ የኦሮምያ ክልል አላስረክብም የሚባለው ትክክል አለመሆኑን የሚገልጹት አቶ አዲሱ፣ ለሶማሊ ክልል ያልተላለፉ ቀበሌዎች አሉ እንኳን ቢባል በድርድር መፍታት እየተቻለ፣ “በኦሮሚያ ክልል 5 ዞኖች ስር በሚገኙ 16 ወረዳዎች በታጠቀ እና በተደራጀ ኃይል ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል በኃይል የአስተዳደር ወሰን ጥያቄን ለመፍታት መሞከር ኢ- ህገመንግስታዊ ነዉ” ብለዋል።
አቶ አዲሱ ይህን ምላሽ የሰጡት አይጋ ፎረም የተባለ የህወሃት ድረገጽ፣ በሁለቱ ድንበሮች ላይ ለደረሰው እልቂት የኦሮምያ ምክር ቤትን ተጠያቂ የሚያደርግ ጽሁፍ ይዞ መውጣቱን ተከትሎ ነው። አቶ አዲሱ ኦህዴድ እራሱን ያጥራ በሚል ከድረገጹ ለቀረበው አስተያየት ሲመልሱ ደግሞ “ ጨፌዉንም ሆነ የክልሉን ካቢኔ በሚሆነዉ ልክ እና ሞዴል መስፋት የሚችለዉ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ነዉ፡፡ ለኦሮሞ ህዝብ ጨፌዉንም ሆነ የክልሉን አስፈጻሚ aigaforum ወይም ማንም ሌላ አካል በፈለገዉ ሞዴል እና መጠን ( size ) ሊሰፋለት አይችልም፡፡ መመኘት ይችል ይሆናል፡፡ ቢመኝም ግን ጉዳዩ ከምኞት የዘለለ አይሆንም፡፡” ብለዋል።
ህወሃት በግልጽ ከሶማሊ ክልል ጎን ቆሞ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት እንዲነሳ ማድረጉን ኢሳት ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወሳል። በህወሃት እና በኦህዴድ፣ በህወሃትና በብአዴን አባላትና አንዳንድ በመካከለኛና በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ አመራሮች መካከል ያለው አለመተማመን እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።