የህውሃት የበላይነት አለ ያሉ በብአዴን አመራር ስብሰባ ላይ በልዩነት የወጡ አመራሮች ከኃላፊነት ተነሱ

መጋቢት ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በክልሉ የብአዴን ውይይት እና የካቢኔ አመራር ስብሰባ ላይ “ የህወሃት የበላይነት አለ” በማለት በልዩነት የወጡ የክልል አመራሮች ከስልጣን ተባረዋል። የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ም/ኃላፊ አቶ ቹቹ እና የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ የሻምበል በውይይቱ ላይ “ ህወሃት አገሪቱን በበላይነት እየመራት ነው፣ ሌሎች ፓርቲዎች ያላቸው ኃላፊነት በእጅጉ የወረደ ነው” የሚል ሃሳብ በማንሳት ሞግተዋል። በክልሉ ካቢኔ፣ “ ድርጅቶች ሁሉ እኩል ናቸው” የሚል የመግባቢያ ሃሳብ ሲሰነዘር ፣ “ የለም ይህንን አንቀበልም ፤ ህውሃት በሀገሪቱ ደህንነት ፣ ፋይናንስ ፣ መገናኛ፣ ወታደራዊ አሰራሮችን ቆልፎ ይዞ ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትግራይ እንዲተሙ ደላላ አስቀምጦ እየሰራ ህወሃትና ሌሎች ድርጅቶች እኩል ናቸው ብትሉን አንቀበልም” የሚል መልስ ሲሰጡ በቃለ ጉባኤው ላይ በልዩነት ሰፈሮላቸዋል፡፡
ንግግሩ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮችን በእጅጉ በማስቆጣቱ ባለስልጣኖቹ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የተጠየቁት ምንጫችን ፣ “ ኢህአዴግ ተናገር ይላል፣ ስትናገር ይገድላል፡፡ ደርግ ደግሞ አትናገር ይላል ስትናገር ይገድላል፡፡ ከሁለቱ የተሻለው የትኛው ነው?” ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል።
በሌላ በኩል ብአዴን ለአራት ቀናት ያካሄደውን ውይይት አጠናቀዋል።
‹‹አምስቱን ተላላፊና ገዳይ ፖለቲካዊ በሽታዎች ከነመንስኤዎቻቸው በመዋጋት ድርጅታችንን በቀጣይነት እናድስ ›› በሚል መሪ ቃል የአራት ቀናት ውይይቱ የተካሄደ ሲሆን፣ በወይይቱ በዕድሜ ዘመን እና በምርጫ ጉዳይ ከማዕካላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው የተገለሉ የቀድሞው የብአዴን አመራሮች ተጋብዘው እንዲናገሩ ተደርጓል።
‹‹በብአዴን አመራር የተፈፀሙ ጥፋቶች›› በሚል ርዕስ አቶ አለምነው መኮንን ባቀረቡት ንግግር፣ የብአዴን አመራር ጥፋት በመፈፀሙ ፣ ከህዝባዊ ወገንተኛነት በመለየቱ እና ላልተገባ ጥቅም ስልጣኑን በማዋሉ የህዝብ ሰላም ታውኳል፡፡ የህገ የበላይነት ተጥሷል፣ የገጠር እና የከተማ ልማት ተስተጓጉሏል፡፡ የትምህርት እና የጤና ልማት አገልግሎት እና ጥራት ወደ ኃላ ቀርቷል፡፡ የዴሞክራሲ አሰተሳሰብ ተቀይዷል፡፡ በተበራከተው የድርጅት እና የአመራር ድክምትም በህይዎት እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡” ብለዋል። የደህንነቱን መዋቅር ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ካለበት አንድ የእዝ ስርዓት መከፋፈል እንደሚያስፈልግ ድርጅቱ ማመኑን ገልጸዋል።
ከድርጅታችን ርዕዩተ አለም ጋር በቁልፍ የተዛመዱ እና የቀዳናቸው ናቸው ያሏቸውን፣ ረጅም አመት በስልጣን ላይ የመቆየት ሚስጢር እና ተሞክሮ ያካፈሉት አቶ በረከት ስምኦን ሲሆኑ፣ በጽሁፋቸው የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲ፤ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የተባበሩት ሩሲያ ፓርቲ፣ የጃፓን ሊበራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣ የሲንጋፖር ፒፕልስ አክሽን ፓርቲ፣ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ፣ የህንድ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ እንዲሁም ከመቶ አመት በላይ የመራውን የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲና የብአዴን -ኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት የተሃድሶ ተሞክሮ በሚል ንግግር አቅርበዋል። በዚህ የክፍል ትምህርት ጊዜ በመሰለው የአቶ በርከት አቀራረብ፣ ሁሉም የፓርቲው አመራሮች ማስታወሻ በመያዝ ሲጨናነቁ ታይተዋል፡፡
አቶ በረከት “ ኪራይ ሰብሳቢ ገኖበታል፤ ትምክህት አመራሩን አጥቅቶታል ፣ ርዕዩተ አለማዊ እና ፖለቲካዊ አሰተሳብ ተሸርሽሯል ፣ አድርባይነት እና ፀረ ዴሞራሲያዊነት በድርጅቱ ውስጥ ገንግኗል” በማለት ፍርሃታቸውን ለተሰብሰቢው አካፍለዋል።
አቶ አዲሱ ለገሰ በበኩላቸው፣ አሁን የገባንበት ችግር ኢህአዴግ ትክክለኛ አቅጣጫ ከማመላከት አልፎ ይህንን እውን ለማድረግ አለመቻሉ ነው ብለዋል።
አቶ አዲሱ “ ኢኮኖሚው በአማካኝ በየአመቱ ከ8 በመቶ ያላነሱ እድገት ቢያስመዘግብም፣ በአንድ በኩል እድገቱ ቀጣይነት የሌለውና አንድ ጊዜ ከአምስት በታች ሌላ ጊዜ ከአስር በመቶ በላይ እየወጣ አራምባና ቆቦ በመርገጥ የሚዋዥቅ እድገት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን በዋናነት ከድህነት ለማላቀቅ በየአመቱ ከ7 በመቶ ያላነሰ እድገት ማስመዝገብ ሲገባት እድገቱ ከዚህ በታች በመሆኑ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት አላስቻለም” ብለዋል።