በጎንደር ከተማ በእግር ኳስ ደጋፊዎችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል ግጭት ተነስቶ ጨዋታው ተቋርጦ ነበር ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 4 ፥ 2009)

እሁድ በጎንደር ከተማ በኢትዮጵያ ቡናና በፋሲል ከነማ መካከል የተካሄደ የእግር ኳስ ጨዋታ በደጋፊዎችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል ግጭት በማስነሳት ጨዋታው ለጥቂት ጊዜያት እንዲቋረጥ ማድረጉን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታው በጎንደር ከተማ ስታዲየም በመካሄድ ላይ እንዳለ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የተለያዩ መፈክሮችን ማሰማት በጀመሩ ጊዜ በድርጊቱ ቅሬታ የተሰማቸው የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃ ለመውሰድ ሙከራ አድርገው እንደነበር ታውቋል።

የጸጥታ ሃይሎች ከደጋፊዎች ሲሰሙ የነበረን መፈክር ለማስቆም በተንቀሳቀሱ ጊዜ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንዲቋረጥ ተደርጎ ሊቀጥል መቻሉን በስፍራው የነበሩ እማኞች አስረድተዋል።

ይሁንና የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንዲቀጥል ቢደረግም ደጋፊዎች የተለያዩ መፈክሮችን ማሰማት እንደቀጠሉ ታውቋል።

በጎንደር ከተማ ተገኝተው የነበሩ የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች በበኩላቸው ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ባህር ዳር ከተማ በመመለስ ላይ እንዳሉ ጠዳ ከተማ ላይ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እማኞች አክለው አስረድተዋል።

በጎንደር ከተማ ሲካሄድ የነበረውን የደጋፊዎች መፈክር የሚያሳይ ቪዲዮም ለዝግጅት ክፍላችን ደርሷል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተካሄድ ጨዋታ በቡና አሸናፊነት 4 ለ1 ቢሆነ ውጤት ተጠናቋል።