መጋቢት ፩ (አንድ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ህዳር ወር የስራ ማቆም አድማ መተው የነበሩት የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች፣ ከአድማው በሁዋላ ችግራቸው እንደሚፈታላቸው ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም በችግር እየተሰቃዩ መሆኑን ገልጸዋል።
“መድረሻ አጥተናል፣ መቆሚያችንን ለሰላም ባስ ለሚባለው ለቀን ወጥተናል። የሰቀቀን ኑሮ ነው የምንኖረው” የሚሉት አሽክርካሪዎች ዳኝነት ጠፍቷል በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል። ኢህአዴግ የጥፋት ሪከርድ ምዝገባ ተወግዷል ቢልም የገንዘብ ቅጣቱ ጨምሮ በመምጣቱ አሽከርካሪዎች ዳግም ወደ ስራ ማቆም አድማው ሊገቡ እንደሚችሉ ምልክቶች እየታዩ ነው።
በሌላ በኩል በቅርቡ የተደረገውን የትራንስፖርት ተመን በመቃወም በሰሜን ሸዋ ዞን በሬማ፣ በመርሃቤቴ፣በሚዳ የአሽከርካሪዎች አድማ ተጀምሯል።ከሬማ መርሃቤቴ፣ከሚዳ ሬማ፣ መርሃቤቴ መራኛ የሚሰሩ መኪኖች በመቆማቸው ከመርሀቤቴ መራኛ የሚሄዱ የህዝብ ተሽከርካሮዎች ባለመኖራቸውው ህብረተሰቡ ለከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ተጋልጧል።