ዶ/ር መረራ ጉዲና የጠየቁት የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2009)

ዶ/ር መረራ ጉዲና የተመሰረተባቸው ክስ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ሊያሰጥ የሚችል ነው በማለት ፍርድ ቤት ያቀረቡትን የዋስትና መብት ጥያቄ አርብ ውድቅ አደረገ።

የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር መረራ ለፍርድ ቤት ያቀረቡትን የዋስትና መብት ጥያቄ በመቃወም ሃሙስ ለፍርድ ቤቱ ባለሁለት ገፅ የተቃውሞ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። አርብ በዚሁ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት የተሰየመው ችሎት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሩ ያቀረቡትን የዋስትና መብት ውድድቅ ማድረጉ ታውቋል።

ዶ/ር መረራ የቀረቡባቸውን የተለያዩ ክሶች እንዳልፈጸሙ በመግለጽ፣ በህገ መንግስቱ የተቀመጠው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ለፍ/ቤቱ ጥያቄን አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ህገመግስታዊ ስርዓቱን በሃይል የመናድ ሙከራ በመሆኑ በዋስትና ቢለቀቁ መረጃ ሊያሸሹና ከሃገር ሊወጡ ይችላሉ በሚል ጥያቄውን ተቃውመዋል። የሁለቱን ወገኖች ጉዳይ በተመከለተ የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተጠርጣሪው በተከሰሱበት የህግ አንቀጽ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ15 አመት በላይ አልያም በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ከመሆኑ በላይ ዋስትናው ተቀባይነት የለውም ሲል ብይን ሰጥቷል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ በዚሁ የክስ መዝገብ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋን እንዲሁም የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሃላፊንና ድርጅቱን እንዲሁም ኢሳትን በተመሳሳይ እና በሽብር ወንጀል መመስረቱ ይታወሳል።