ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ብር ባለፉት 12 ወራቶች ብቻ የመግዛት አቅሙ ከአምስት በመቶ በላይ ማሽቆልቆሉን አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አስታወቁ።
የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ መምጣት በህብረተሰቡ ላይ ከሚያደርሰው የኢኮኖሚ ተፅዕኖ በተጨማሪ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና የዋጋ ግሽበት እየተፈታተነ እንደሚገኝም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
መንግስት አጋጥሞት ያለውን የፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ እንዲሄድ ካደረጉ ምክንያቶች ዋንኞቹ ሆነዋል።
በኬንያ በሚገኘው የሳይቶን ኢንቨስትመንት ማኔጅመንት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ሞሪስ አዱር በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፋይናንስ እና የብር አቅርቦት ችግር ተከትሎ 10 የውጭ ሃገር ባንኮች በሃገሪቱ ወኪል ቢሮን በመክፈት ብድር በማቅረብ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ብሉምበርግ የዜና አውታር ገልጸዋል።
ይሁንና መንግስት ባንኮቹ በሙሉ የባንክ አገልግሎት ስራ ላይ እንዳይሰማሩ እገዳን ጥሎ እንደሚገኝ የተናገሩት ባለሙያው በርካታ ባንኮች እገዳው እንዲነሳ የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል
በሃገሪቱ የፋይናንስ እጥረት ተጽዕኖን እያደረሰ እንደሆነ የገለጹት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎ በዋቢነት ባለፉት 12 ወራቶች ብቻ የብር የመግዛት አቅም በ5.3 በመቶ መቀነሱን ለዜና አውታሩ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ እድሚያቸው ከ18 በላይ ከሆኑት ህዝቦች መካከል 22 በመቶ ብቻ የሚሆነው የባንክ አካውንን ያለው ሲሆን፣ ቁጥሩ በሰብ ሰሃራ አፍሪካ በአማካኝነት ከተቀመጠው 34 በመቶ እጅጉኑ ያነሰ መሆኑም ተመልክቷል። በአፍሪካ በኢኮኖሚ እድገቱ ግንባር ቀደም እንደሆነች በሚነገርላት ደቡብ አፍሪካ 70 በመቶ ዜጎቿ የባንክ አካውንት እንዳላቸው ብሉምበርግ በዘገባው አስፍሯል።
የአለም ባንክ የኢትዮጵያ የብድር ክምችት እየጨምረ መምጣት በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ጫናን እንደሚያሳድር አስታውቆ መንግስት ብድርን የመውሰድ ፖሊሲ እንዲፈትሽ ስያሳስብ ቆይቷል።
የመንግስት በብቸኝነት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ፕሮጄክቶች በዜጎች ላይ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖን እያሳደረ ይገኛል ያለው ባንኩ የግል ባለሃብቶች በልማት እንቅስቃሴው ተሳታፊ ቢያደርግ ችግሩን መቀነስ እንደሚቻል ጠቁሟል።
ባለፈው አመት በሃገሪቱ ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃሞ በኢኮሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖን በማሳደር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በአምስት በመቶ አካባቢ እንዲቀንስ ማድረጉን ብሉምበርግ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት መረጃ ዋቢ በማድረግ በዘገባው አቅርቧል።
ኢትዮጵያ አጋጥሟት ያለው የፋይናንስ ችግር ለአመታት ዝግ አድርጋ የቆየችውን የባንክ ፖሊሲ እንድታሻሽልና በቅርቡ ለውጭ ባንኮች በሙሉ የባንክ ስራ ላይ እንዲሰማሩ በሯን እንደምትከፍት ኤክስ አፍሪካ ቤስሊንግ የተሰኘ የፋይናንስ ተቋም ገልጿል።