የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ድርድሩ እንደማይሳካ እየገለጹ ነው።

የካቲት ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ፣ አማራና ደቡብ አካባቢዎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በአገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር እነጋገራለሁ ያለው ኢህአዴግ፣ ለእውነተኛ ድርድር ከልቡ ያልተዘጋጀ በመሆኑ ድርድሩ እንደማይሳካ፣ በምርጫ 97 ወቅት “ከኢህአዴግ ጋር መስራት ይቻላል” ብለው ከቅንጅት ወጥተው ለ5 ዓመታት የፓርላማ አባል ሆነው ያገለገሉት አቶ አብዱረህማን አህመዲን ተናግረዋል። ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በየነም ድርድሩን አጣጥለውታል።
ስለድርድሩ ጠቀሜታ እንዲናገሩ የተጠየቁት አቶ አብዱረህማን ፣“ከዚህ በፊት ከኢህአዴግ ጋር በተደረጉ ድርድሮች ተሳትፌአለሁ፣ ድርድሮቹ ሁሉ የይስሙላ ናቸው። ኢህአዴግ ‘ ሰጥቶ መቀበል’ ይልሃል፣ ነገር ግን ኢህአዴግ መቀበል እንጅ መስጠት የሚባል ነገር አያውቅም። ይዞት ከመጣው አንዲት ቃል ለምሳሌ ነበር የሚለውን ፣ ነው በሚል እንተካው ብትለው ፈቃደኛ የማይሆን ድርጅት ነው። እንዲህ አይነት አመለካከት ይዞ ከሆነ አሁንም የመጣው ድርድሩ ቢቀር ነው የሚሻለው፣ ጉልበታቸውንም ጊዜያቸውንም ባያባክኑ ይሻላል ” በማለት ፣ ከኢህአዴግ ጋር መደራደር ይቻላል በማለት ለረዘም ያለ ጊዜ የያዙትን አቋም የሚቀይር ንግግር ተናግረዋል
“ተቃዋሚዎችም ባህሪያቸውን እየለዋወጡ አስቸግረዋል” ያሉት አቶ አብደሩህማን፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሬሳ ሳጥን ውስጥ ገብቷል ሲሉ በሰላማዊ ትግል ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸዋል። “ህገመንግስትን ያልተቀበሉ ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማያደርጉትንም በድርድሩ እንዲሳተፉ እድሉ ሊመቻችላቸው ይገባል” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
“ኢህአዴግ ሁሉንም በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችንም እንዲጠራ” አስተያየት የሰጡት ፕ/ር በየነ ደግሞ፣ ኢህአዴግ ባልተማሩ ካድሬዎቹ ሲያስቸግረን እንደኖረ አሁንም እያስቸገረን ይቀጥላል ብለዋል። “ እኛ በህዝብ እየተወቀስን፣ ስማችን እየጎደፈ መቀጠል አንፈልግም” የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ የታሰሩ የህሊና እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ ጠይቀዋል። “ እኛም ድርድር እያልን ህዝቡን አሰለቸን” ያሉት ፕ/ር በየነ፣ “ ስልጡን ባልሆነ ካድሬ እየተሰቃየን ነው” ሲሉም ያክላሉ።
“ኢህአዴግ የእጁን ያገኘ ድርጅት ነው” ያሉት ፕ/ር በየነ፣ በቅርቡ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የምርጫ 97 ንዴት የወለደው መሆኑንም ገልጸዋል። “ ህዝቡ ሞት ሳይፈራ ደረቱን ለጥይት እየሰጠ ነው” የሚሉት ፕሮፌሰሩ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እንዲፈቱ እንዲሁም በአገር ውስጥም ያሉና የሌሉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችም በድርድሩ እንዲካተቱ ጠይቀዋል።