በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች የተቀሰቀሰውን የመምህራንን ተቃውሞ እንደሚደግፍ መቀመጫውን በውጭ አገር ያደረገ የኢትዮጵያ መምራን ማህበር አስታወቀ

ኢሳት (የካቲት 30 ፥ 2009)

መንግስት ሰሞኑን ያደረገው የደሞዝ ማስተካከያ መምህራንን ያካተተ አይደለም በማለት በምስራቅ ጎጃምና በወሎ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ መምህራት የስራ ማቆም አድማን እንደሚደግፍ መቀመጫውን በውጭ ያደረገው የኢትዮጵያ መምራን ማህበር ለኢሳት አስታወቀ።

መምህራኑ ከሁለት ቀን በፊት የስራ ማቆም አድማቸውን በመጀመር ጥያቄን ማቅረብ ቢጀምሩም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ምላሽ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ የማህበሩ ሰብሳቢ ኮሚቴል ሊ/መንበር አቶ ካሳሁን ከበደ ገልጸዋል።

መንግስት በቅርቡ የተደረገው የደሞዝ ማስተካከያ የተወሰኑ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞችን ብቻ የሚመለከት እንደሆነም ማስታወቁ ይታወሳል።

ይሁንና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ መምህራን የተወሰደው ዕርምጃ መምህራንን ያካተተ አለመሆኑ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃውሞ ማቅረብ መጀመራቸውን መምህራኑና የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።

በተለይ በጎንደር፣ ምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በወሎ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚያስተምሩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን በስራ ማቆም አድማ ውስጥ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

የመብት ጥያቄን እያቀረቡ ያሉት እነዚሁ መምህራን በጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካላት ለጥያቄያቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸው በተለያዩ መንገዶች እያቀረቡ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ሃላፊዎች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

ጥያቄው የመብት ጥያቄ ነው የሚሉት አቶ ካሳሁን ከበደ መምህራን በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ጥያቄን ሲያቀርቡ ቢቆዩም በቂ ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸውን ማህበሩ አውስቷል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በሃገሪቱ ያሉ መምህራን በአመቱ መጀመሪያ የደሞዝ ማስተካከያ የተደረገላቸው በመሆኑን በአዲሱ ማስተካከያ ሊካተቱ አለመቻላቸውን አቶ ካሳሁን አክለው ተናግረዋል።

የመምህራኑ ጥያቄ መነሻው ከደሞዝ ጭማሪ አልያም ከማስተካከያ ጋር የተገናኘ ቢሆን፣ የዴሞክራሲ መብት ድምፅን ያነገበ እንደሆነ በውጭ የሚገኘው የኢትዮጵያ መምህራን ሰብሳቢ ኮሚቴ ሊቀመንበር በቃለ-ምልልሳቸው አስታውቀዋል።

ይኸው የመምህራን የዴሞክራሲ መብት ጥያቄ በተማሪዎችና ወላጆች እንዲሁም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፍ እንዳለበትም ሰብሳቢው ገልጸዋል።

በሃገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነት በማካካስ ታስቦ የተወሰኑ የመንግስት ሰራተኞች በአዲሱ የደሞዝ ማስተካከያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የመንግስት ባለስልጣናት ከቀናት በፊት ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

ይሁንና ተቃውሞ እያቀረቡ ያሉ መምህራት የኑሮ ውድነቱ እነሱንም እየነካ ያለ ጉዳይ በመሆኑ መምህራን ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው ጥያቄን አቅርበው ይገኛል።