የኢህአዴግ መንግስት ወደ ፖለቲካና የህሊና እስረኞችን አማላጅ መላኩ ተነገረ

የካቲት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ ወደ እስር ቤቶች ሽማግሌዎችን የላከው በቅንጅት ጊዜ እንዳደረገው የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይቅርታ ጠይቀው እንዲፈቱ በሚል ነው።
በዚህም መሰረት ኢህ አዴግ የተመረጡት ሽማግሌዎች ወደ እስር ቤት በማምራት የአንድነት ፓርቲ አመራሩን አቶ አንዱአለምን አራጌን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን እና ሌለኛውን የአንድነት ፓርቲ አባል አቶ ናትናኤል መኮንን በጉዳዩ ዙሪያ እንዳነጋገሯቸው የእስር ቤት ምንጮች ገልጸዋል።
ይሁንና በትናንትናው ዕለት የኅሊና እስረኞቹን ለማግባባት የተላኩት ሰዎች ጥረታቸው ሳይሳካ ተመልሰዋል። ለሽማግሌዎቹ በውይይታቸው ላይ እስረኞቹን “ይቅርታ ጠይቁና ከወህኒ ውጡ” ብለው ሲጠይቋቸው እስረኞቹ “እኛ ይቅርታ የምንጠይቅበት ምክንያት የለም። ላልፈጸምነው ጥፋት ይቅርታ አንጠይቅም።ከፈቱን እንዲሁ ይፍቱን። ይቅርታ የሚባለውን ነገር ፈጽሞ አናደርገውም”የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።
ሽማግሌዎቹ ከሁሉም የኅሊና እስረኞች ተመሣሳይ ምላሽ ማግኘታቸው ታውቋል።