የካቲት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የክልሉ ካቢኔ አወቃቀር በዘር ማንዘር የተዋሀደ እና እውቀትን እና ትምህርትን ያላገናዘበ ባለመሆኑ ክልላችን ላይ ችግር ደቅኗል ያሉት ጋዜጠኞች፣ ብአዴንን ለአማራ ህዝብ ያልሆነ አሻንጉሊት ነው ብለውታል፡፡
ጋዜጠኞች ከየካቲት 24 2009 ጀምሮ ለመጭው ቀናት በሚቀጥለው ውይይታቸው እየተካሄደ ያለው “ጥልቅ ተሃድሶ ሳይሆን ጠቅ ትሃድሶ ነው” ብለውታል፡፡ “እንደ አማራ የሚያስብ ድርጅት በሌለበት አማራ በተገለለበት ሀገር እና ህዝብ ብአዴን በጋዜጠኝነት ነፃነታችን የሙዚቃ ምርጫ እንኳን እጁን ባስገባበት ሁኔታ ፣ እኛየህውሃትን የበላይነት እያየን ከእናንተ በበለጠ መረጃ እና የህዝብ ብሶት እየሰማን የምንኖር ሰዎችን ልታታሉን የምትቸሉበት አቅም የላችሁም፡፣ሳይመሽባችሁ አሁን የታፈነው እረመጥ አንድ ቀን እንደቋያ እሳት መንደዱ ስለማይቀር መልክ አልባ ያደረጋችሁትን ህዝብ በፍጥነት ይቅርታ ጠይቃችሁ ራሳችሁን አድኑ” ብለዋቸዋል፡፡
በዚህ ከፍተኛ የብአዴን አመራሩን አንገት ባስደፋው መድረክ ፤የ15 ዓምታት የኢህአዴግ ስኬታማ ጉዞ ተብሎ በቀረበው ፅሁፍ ላይ ተንተርሰው የአማራ መታረድ ፤ መገደል ፤ የባለስልጣናቱን ሙስኛነት እና አቅም ማነስ የህዝቡን እምቢተኛነት ፤ አንሰተው ያቀረቡትን መረጃ አጣጥለውታል።
ዘጋቢያችን ምንጮቿን ዋቢ አድርጋ እንደዘገበችው ጋዜጠኞቹ፣ “ የወልቃይትን ጉዳይ እንዳንዘግብ ተከልከለናል፣ አንደበታችን ታፍኗል “ ያሉ ሲሆን፣ የሚዲያው የቦርድ ሰብሳቢ እና የአማራ ክልል ኮምኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ወልቃይትን በተመለከተ ብአዴን በምንም ተአምር እንደማይመለከተው ተናግረዋል፡፡
በአመራር አመዳደብም የብአዴን መሪ አቶ አለምነው መኮንን ሚዲያውን ለመቆጣጠር እንዲያመቸው የአገሩ ልጅ የሆነውን የቀድሞ የደሴ ከንቲባ አቶ አለባቸው የሱፍን ኃላፊ አድርጎ ከሙያው ውጭ የሾመ ሲሆን፣በምክትል ስራ አስኪያጅነት የሚመሩት አቶ መሉቀን ሰጥየ የብአዴን ተላላኪና የአቅም ችግር ያለበት በመሆኑሚዲያውን የግሉ ፍላጎት ማርኪያ እና የውጭ መጓጓዥ እያደረገ ስለሆነ ይውረድልን የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡በግምገማ ብአዴን የተዋረደበትን ይህን መድረክ አስመልክቶ በቀጣይ በልዩ ፕሮግራም እና ዜና እወጃዎቻችን ሰፊ መረጃ ይዘን እንመለስበታለን፡፡