ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2009)
መምህራንን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞች በቅርቡ ተደርጓል የተባለውን የደሞዝ ጭማሪ ተግባራዊ አልተደረገልንም ሲሉ ተቃውሞ አቀረቡ። በአንዳንድ አካባቢዎች የመምህራን አድማ ተጀምሯል።
በተለይ በጎጃምና በጎንደር አንዳንድ መምህራን አድማ አስነስታችኋል በሚል እየታሰሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። አድማው ከደሞዝ ማስተካከያ የተያያዘ ነው ቢባልም፣ አጠቃላይ የነጻነት ጥያቄን ያዘለ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በጎጃም በተለያዩ ወረዳዎች ማለትም ዱርቤቴ፣ ቁንዝላ፣ ይስማላ፣ እና አሹዳ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩም በሰሜን ወሎ በደላንታ፣ በመካነሰላም፣ በደቡብ ወሎ ምዕራብ ወረዳዎች መምህራን አድማ መምታታቸው ታውቋል።
ከተለያዩ ሰራተኞች የቀረበውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ረቡዕ ማብራሪያን የሰጡ የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ባለፈው ወር የተደረገው ውሳኔ የደሞዝ ስኬል ማስተካከያ እንጂ የደሞዝ ጭማሪ አይደለም ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል። የመንግስት ሰራተኞች በተለይ መምህራን ማስተካከያ ቢሆንም እኛን ማካተት ይኖርበታል ሲሉ ቅሬታቸውን እያቀረቡ ይገኛል።
የመንግስት የደሞዝ ማስተካከያ ከዚህ ቀደም ከሌላው የመንግስት ሰራተኛ ከፍ ያለ የደሞዝ ስኬል ያላቸው ተቋማትን አይመለክተም ብሏል።
የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በጥር ወር 2009 እና በሃምሌ ወር 2008 አም ለመምህራን የጸደቀው ማሻሻያ የደሞዝ ስኬል ማስተካከያ እንጂ ጭማሪ አለመሆኑን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቋል። በተያዘ በጀት አመት መጀመሪያ ዳኞች፣ መምህራን፣ አቃብያነ ህግ፣ የአካዳሚ ሰራተኞችና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የስኬል ማስተካከያ እንደተደረገላቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።
እነዚሁ ሰራተኞች ባለፈው ወር በተደርገው ማስተካከያ አለመካተታቸውንና በአጠቃላይ 33 መንግስታዊ ተቋማት በአዲስ ማስተካከያ አለመታቀፋቸው ታውቋል።
አዲስ ማስተካከያም የፖሊስና መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የህዝብ ተመራጮችን እንዲሁም ተሿሚዎችን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
የተወሰደው ዕርምጃም በተሟላ ጥናት ላይ የተመሰረተና የመንግስት የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ሲል የሚኒስቴሩ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
መምህንራንን ጨምሮ በአዲሱ ማስተካከያ ያልተካተቱ ሰራተኞች በበኩላቸው የኑሮ ሁኔታ ለማገዝ የተደረገ ነው የተባለው ማስተካከያ እነሱንም ማካተት እንዳለበት ቅሬታን እያቀረቡ እንደሆነ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
መንግስት በበኩሉ በተለይ ለመምህራን የተደረገው የደሞዝ ማስተካከያ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ማስተካከያው የመምህራን የሰው ሃይል የመቅረፅ ተልዕኮ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው በማለት ምላሽን ሰጥቷል። ይሁንና ጥያቄውን እያቀረቡ ያሉት መምህራን በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር አዲሱ ማስተካከያ እነሱንም ማካተት እንዳለበት ይገልጻሉ።