በኢትዮጵያ የነበሩ ወደ 9 ሺ የሚጠጉ ቤተ-እስራዔላውያን ወደ እስራዔል እንዲጓጓዙ ተጠየቀ

ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2009)

የእስራዔል የፓርላማ አባላት የሃገሪቱ መንግስት በጎንደርና አዲስ አበባ ከተሞች የሚገኙ ወደ ዘጠኝ ሺ አካባቢ ቤተ-እስራዔላዊያን በአስቸኳይ ወደ እስራዔል እንዲጓጓዝ አሳሰቡ።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ በመገኘት የቤተ-እስራዔላውያን ሁኔታ የተመለከቱ አራት የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት በጎንደርና አዲስ አበባ ከተሞች ያዩት ሁኔታ እጅግ አስደንጋጭ መሆኑን እንደገለጹ ጀሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ የፓርላማ አባላቱን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በእስራዔል መግለጫን የሰጡት የፓርላማ አባላቱ በሁለቱ ከተሞች የሚገኙት ቤት እስራዔላውያን በምግብና መድሃኒት አቅርቦት ሳይቀር በችግር ውስጥ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የእስራዔል መንግስት ለበርካታ አመታት ቤተሰቦቻቸውን ለመቀላቀል በመጠባበቅ ላይ የሚገኙትን እነዚሁ ዘጠኝ ሺ አካባቢ ቤተ-እስራዔላውያን ያለምንም መዘግየት በአስቸኳይ ወደ እስራዔል እንዲጓጓዙ የፓርላማ አባላቱ ጥያቀን አቅርበዋል።

ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ዘጠኝ ሺ የሚሆኑት ቤተእስራዔላውያን በቅርቡ መጓጓዝ እንደሚጀምሩ ይፋ አድርገው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና የተገባውን ቃል ተከትሎ ጉዳያቸው ተጠናቆ በፈረንጆቹ 2016 አም እስራዔል መጓዝ የቻሉት 63 ቤተ-እስራዔላውያን ሲሆኑ የእስራዔል መንግስት የገባውን ቃል ተግባራዊ አላደረገም ሲሉ የፓርላማ አባላቱ ቅሬታቸውን እንዳቀረቡም ጀሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።

ሜየር ኮህን የተባሉ የፓርላማ አባል በጎንደርና አዲስ አበባ ከተሞች ባደረጉት ጉብኝት የቤተ-እስራዔላውያኑ ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ መሆኑንና የእስራዔል መንግስት ሊያፍር የሚገባው ነው ሲሉ ለጋዜጣው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉ የፓርላማ አባላት ይኸው ሁኔታ በቅርቡ በፓርላማ ቀርቦ ውይይት እንዲካሄድበት እንደሚደረግም አክለው አስታውቀዋል።

ከአውሮፓ ሌሎች ተመሳሳይ ስደተኞች ወደ እስራዔል እየተጓጓዙ ባለበት ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙት ቤት እስራዔላውያን ጉዞ መጓተቱ ጥያቄ ሊሆን ይገባል ሲሉ ኮህን ተናግረዋል። በእስራዔል የሚኖሩ በርካታ የኢትዮጵያ ቤተ-እስራዔላውያን በተለያዩ ጊዜያት ሰላማዊ ሰልፎችን በማካሄድ ቤተሰቦቻቸው እንዲጓጓዙ ጥያቄን ሲያቀርቡ መቆየታቸው አይዘነጋም።

ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎ የሃገሪቱ ፓርላማ ወደ ዘጠኝ ሺ አካባቢ የሚሆኑት በአስቸኳይ እንዲጓጓዙ ውሳኔን ቢያስተላልፍም የቤተ-እስራዔላውያኑ ጉዞ ከተጠበቀው በላይ መጓተቱን የእስራዔል ባለስልጣናት በመግለጽ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።