በደቡብ ሱዳን የዘር ማጥፋት ድርጊት ሊፈጸም ከጫፍ መደረሱን ተመድ ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2009)

በረሃብ አደጋ አጋጥሟት ባለው ደቡብ ሱዳን የዘር ማጥፋት ድርጊት ከጫፍ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረቡዕ ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት አስታወቀ።

በሃገሪቱ ባለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ ለሰባት ወር የፈጅት ጥናት ማካሄዱን የገለጸው ድርጅቱ፣ በደቡብ ሱዳን በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለውን ግጭት ምክንያት በማድረግ በፕሬዚደንት ሳልባኪር የሚመራው መንግስት በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት እየወሰደ እንደሚገኝ አጋልጧል።

የሃገሪቱ ብሄራዊ የደህንነት አገልግሎት፣ ፖሊስ እንዲሁም ሌሎች ታጣቂዎች ይህንኑ ድርጊት በተቀናጀ መልኩ እየፈጸሙት ነው ያለው የተባበሩት መንግስታ ድርጅቱ በተወሰኑ አካባቢዎች ሰው ሰራሽ ረሃብ እንዲከሰት መደረጉንም በሪፖርቱ አስፍሯል።

አብዛኛውን የመንግስት አስተዳደርና ስልጣን ይዘው የሚገኙት የዲንቃ ጎሳዎች በተለይ በንዌር ማህበረሰብ ላይ የዘር ማጥፋት የተባለውን ድርጊት እየወሰዱ እንደሆነ ተመልክቷል። መንግስት የድርቅ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች እርዳታ እንዳይደርስ ክልከላ ማድረጉ ረሃብ እንዲከሰትና ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት መሆኑንም በሪፖርት ተገልጿል።

ይኸው አለም አቀፍ ሪፖርት በተለይ በሃገሪቱ ባለው አለም አቀፍ ሪፖርት በተለይ በሃገሪቱ ባለፈው አመት በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የፕሬዚንት ሳልባኪር መንግስት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም መቆየቱንና ድርጊቱ ዘር ማጥፋት ጫፍ መድረሱን  ተመድ ይፋ አድርጓል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከወራት በፊት ተመሳሳይ ስጋትን በመግለጽ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዕርምጃን እንዲወስድ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።

የፕሬዚደንት ሳልባኪር መንግስት በበኩሉ ሪፖርቱን በማስተባበል በሃገሪቱ ያለውን ግጭት ዕልባት ለመስጠት ብሄራዊ ድርድር መጠራቱን ገልጸዋል።

ይሁንና የአማጺ ቡድን አመራሮችና ሌሎች አካላት ብሄራዊ ድርድሩ ሁሉንም ያሳተፈ አይደለም በማለት መንግስት አካሄጄደዋለሁ የሚለው ድርድር እና ውይይት ውጤት እንደማያመጣ በመግለጽ ላይ ናቸው።

በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን ከመንግስት ጋር የደረሰው ስምምነት ውድቅ መሆኑን ተከትሎ በአዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን ያለ ግጭት እየተባባሰ መምጣቱ ይታወቃል። ኢትዮጵን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የደቡብ ሱዳን መንግስት በሪክ ማቻር ከሚመራው አማጺ ቡድን ጋር ስምምነት እንዲደርስ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ሁለቱ ወገኖች የጋራ  ብሄራዊ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ማቻር የምክትል ፕሬዚደንት ስልጣን መረከባቸው የሚታወስ ነው።

ይሁንና በሁለቱ ወገኖች በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን ግጭት ስምምነቱን እንዲያከትም ያደረገ ሲሆን፣ ሪክ ማቻርም ከሃገራቸው በመሰደድ በደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ።

የአዲሱ ግጭት መቀስቀስን ተከትሎም ኢትዮጵያ በሃገሯ አቆይታቸው የነበሩት ሪክ ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳን ጥላለች። የአማጺ ቡድኑ አመራሮች በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዕርምጃ በድርድሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን በመግለጽ ላይ ናቸው።