የካቲት ፳፰ ( ሃያ ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዮዲን እጥረት በዋንኛነት የእንቅርት በሽታ የሚያስከትል ከመሆኑም በተጨማሪ የህጻናት የአእምሮ ዕድገት በመጉዳት በዘላቂነት የአምራች ዜጋ እጦትን ያስከትላል፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ ጨው የሚመረትባቸው አካባቢዎች አፋር ክልል ዶቢ እና አፍዴራ ሐይቆች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ኢራካል ሐይቆች በሚገኝ ምርት ነው፡፡ ከሚኒስቴሩ የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ወር ጊዜውስጥ ብቻ 300 ሺ ኩንታል የገበታ ጨው የሚያስፈልግ ሲሆን ከ30 እስከ 40 ሺ ኩንታል ለኢንዱስትሪ የሚውል የጨው ምርት ፍላጎት አለ፡፡የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሄልዚ ኢንስቲትዩት በአዮዲን የበለጸገ ጨው እስከ 88 በመቶ ለማድረስ እየሰራ ነው ቢልም በተግባር ግን አሳዛኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ዩኒሴፍ በአዮዲን እጥረት በዓለም ላይ በከፋ ሁኔታ ከተጠቁ 13 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዱዋ በማድረግ ክትትልና ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡በአምራቾቹ በኩል የጨው ምርትን በአዮዲን ለማበልጸግ የሚውለው ኬሚካል በበቂ ሁኔታ አለማግኘታቸው የችግሩ ምንጭ መሆኑን የሚያስረዱ ሲሆን ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግን ሀገሪቱ በየዓመቱ 10 ሚሊየን ዶላር ለጨው ግብዐት የሚውልኬሚካል ከውጪ ገዝቶ የሚያስገባ መሆኑን በመግለጽ የግብአት እጥረት የለም ሲል ያስተባብላል፡፡በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የእናቶች እና ህፃናት ሞትን እያስከተሉ ያሉት አራቱ ዋና ዋና የምግብ አለመመጣጠን ችግሮች መካከል ከአዮዲን እጥረት ጋር በተያያዘ የሚከሰት የጤና ችግሮች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡