የትራምፕ አስተዳደር  ስደተኞችን በተመለከተ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተላለፈው ውሳኔ በድጋሚ ከህግ አካላት ዘንድ ተቃወሞ ገጠመው

ኢሳት (የካቲት 28 ፥ 2009)

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሰኞ ስደተኞችን በተመለከተ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተላለፈውን ውሳኔ በድጋሚ ከህግ አካላት ዘንድ ተቃወሞ ገጠመው።

ፕሬዚደንቱ በአዲስ መልክ ያወጡትን ውሳኔ የተቃወሞ አካላት ዕርምጃው አሁንም ቢሆን የሙስሊም ሃገራትን ሆን ብሎ ያነጣጠረ ነው ሲሉ ቅሬታን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በዚሁ አዲስ ውሳኔ መሰረት ስድስት ሃገራት ለሶስት ወር ተግባራዊ የሚሆን የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ኢራቅ በአዲሱ መመሪያ እገዳው ነጻ ተደርጋለች።

ይሁንና ከአንድ ወር በፊት የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩት ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና፣ የመን በዚሁ አዲስ ውሳኔ በድጋሚ ኢላማ የሆኑ ሲሆን፣ ኢራቅ የደህንነት እና ቪዛ መረጃዎችን በመለዋወጥ በኩል ማሻሻያን አሳይታለች ተብላ ከእገዳው እንድትወጣ መደረጉን የአሜሪካ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በአዲሱ ውሳኔ መሰረት የሶሪያ ስደተኞች እስከመጨረሻው ድረስ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የተላለፈው ውሳኔ እንዲሻሻል መደረጉንና ሁሉም ስደተኞች ለሶስት ወር ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እገዳ መቀመጡን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በፕሬዚደንት ትራምፕ የተላለፈው ይኸው ውሳኔ ብሄራዊ ደህንነትን ለማጠናከር ያለመና ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ከ10 ቀን በኋላ ተግባራዊ የሚሆነው ይኸው ውሳኔ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውን የስድስቱ ሃገራት ዜጎች የማይመለከት እንደሆነም የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከአንድ ወር በፊት ተግባራዊ አድርገው የነበሩት ተመሳሳይ ውሳኔ የሃገሪቱን ህግ የሚጻረር ነው ተብሎ በፍርድ ቤት ውድቅ መድረጉ ይታወሳል።

ይሁንና ፍርድ ቤት ያስተላልፈውን ውሳኔ ይግባኝ እንደሚጠይቁበት አስታውቀው የነበሩት ፕሬዚደንቱ ውሳኔያቸውን በድጋሚ ተግባራዊ ለማድረግ አሁንም ድረስ ጥያቄ የተሞላበት ውሳኔ ማስተላለፋቸውን የህግ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

የኒው ዮርክ ግዛት ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት ኤሪክ ሺደርማን ፕሬዚደንቱ በድጋሚ ያስተላለፉትን ውሳኔ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት መግለጻቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል። አዲሱ ውሳኔ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን ያካተተ ቢሆንም፣ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረው እገዳ አሁንም ግልፅ አይደለም ሲሉ አቃቤ ህጉ አስረድተዋል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አዲሱ ውሳኔ አሁንም ድረስ ሃይማኖትን ላይ ያነጣጠረ ነው በማለት ተቃውሞን ማቅረብ የጀመሩ ሲሆን፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ዳግም መታገድ እንዳለበት ጥያቄን አቅርበዋል።

የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጄፍ ሴሽን በበኩላቸው ወደ አሜሪካ በስደተኝነት ከገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ከ300 የሚበልጡት በአሁኑ ወቅት ከሽብር ወንጀልና ድርጊት ግሃር በተያያዘ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። ይሁንና አቃቤ ህጉ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በአዲሱ ውሳኔ የጉዞ እገዳ ከተጣለባቸው ስድስቱ ሃገራት መካከለ ሶስቱ በአሜሪካ ለሽብርተኛ ድጋፍን ያድርጋሉ ተብለው የተፈረጁ ሲሆን፣ ሶስቱ ደግሞ ግዛታቸውን ከአልቃይዳና ከአይሲስ ቁጥጥርና ጥቃት ለመከላከል ያልቻሉ እንደሆነ የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች ይገልጻሉ።