በሱዳን የሚኖሩ የሃይማኖት አባትና ሌሎች ስደተኞች ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጡ

ኢሳት (የካቲት 28 ፥ 2009)

በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ለእስር ተዳርገው የነበሩ አንድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባትና ሌሎች ሰዎች ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ጉዳዩን በመከታተል ላይ ያሉ አባላት ለኢሳት አሳታወቁ።

የሃይማኖች አባቱ ቄስ ተገኝ በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ታፍነው ላለፉት 10 ወራቶች ያህል በእስር ላይ እንደነበሩ የተናገሩት እነዚሁ አካላት በሃገሪቱ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የሃይማኖት አባቱን ጉዳት በመከታተል ላይ እንደነበር ከዜና ክፍላችን ጋር ያደረጉ እነዚሁ አካላት ገልጸዋል።

ይሁንና ሰኞ ምሽት የኢትዮጵያ የሰሌዳ ቁጥር ያለው ተሽከርካሪ የሃይማኖት አባቱን እንዲሁም ሌሎች ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ይዞ መሄዱን ጉዳዩን በመከታተል ላይ የሚገኘው በስዊድን የልሳነ-ግፉዓን የወልቃይት ማህበረሰብ ለኢሳት አስታውቋል።

የሃይማኖት አባቱ ቄስ ተገኝ ከዚሁ በፊት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ተወስደው በፍ/ቤት ነጻ ከተባሉ በኋላ ወደ ሱዳን መመለሳቸውንና መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር የማህበረሰቡ ተወካይ አቶ አበራ ለኢሳት አስረድተዋል።

በሱዳን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩት ቄስ ተገኝ በሃገር ቤት ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ጋር በተገናኘ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት በመሸሽ በሱዳን ይኖሩ እንደነበር ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የሃይማኖት አባቱ ቤተሰቦች ቄስ ተገኝ ያሉበትን ቦታና ሁኔታ ባለማወቃቸው በስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ጉዳዩን በመከታተል ላይ ያሉ አካላት ገልጸዋል።

ከሃይማኖት አባቱ ጋር ቁጥራቸው ያልታወቁ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራችሁ ትመለሳላችሁ ተብለው በተሽከርካሪ እንዲሳፈሩ መድረጉንም ለመረዳት ተችሏል።

የአውሮፓ ፓርላማ የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽሙና ከለላ የሚፈልጉ ስደተኞችም ወደ ሃገራችው እንደሚመልስ ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ድርጊቱን የኮነኑ የፓርላማ አባላት የአውሮፓ ህብረት ሱዳን የስደተኞችን ፍልሰት ለመቆጣጠር ሊያደርግላት የሚገባውን የ100 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንዲቋረጥ ጥያቄን ማቅረባቸውን ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።

በቅርቡ የሱዳን መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ ክፍያ እንዲጨምር ማድረጉን ተከትሎ በካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግንኙነቱን ተጠቅሞ ክፍያውን እንዲቀንስ ማግባባት እንዲያደርግ በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይሁንና ሰልፉ የጸጥታ ስጋት ነው በማለት ኤምባሲው የሱዳን የጸጥታ ሃይሎችን በመጥራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለእስር መዳረጋቸው ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም።

ለእስር ከተዳረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል ወደ 60 የሚጠጉት በፍርድ ቤት በ40 የጅራፍ ግርፋት እንዲቀጡ የተደረገ ሲሆን፣ ድርጊቱን የአውሮፓ ፓርላማ አውግዞታል።

ነዋሪነታቸው በሱዳን የሆነ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው የሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች በተለያዩ ጊዜያት የሚደርሱባቸው ወከባና ኢሰብዓዊ ድርጊት እየተባባሰ መምጣቱን ሲገልፅ ቆይቷል።