ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው የሚገኙ ሰዎች በገንዘብ እጥረት የተነሳ የምግብ አቅርቦት እንደማያገኙ ተመድ ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 28 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው የሚገኙ በሚለዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በገንዘብ እጥረት የተነሳ በቂ የምግብ አቅርቦት አለማግኘታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

ለሃገሪቱ የሚያስፈልገው አለም አቀፍ ድጋፍ በወቅቱ ባለመገኘቱ ምክንያት በደቡብ ክልል የህክምና ባለሙያዎችን ማሰማራት አልተቻለም ያለው ድርጅቱ የድርቁ አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለት ወር በፊት ድርቁን ለመቋቋም የአንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የገንዘብ ድጋፍ ጥሪን ቢያቀርቡም ምላሹ አነስተኛ መሆኑ ታውቋል።

የሚፈለገው ድጋፍ ባለመገኘቱ ሳብያ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ተረጂዎች እርዳታን ማግኘት ያልቻሉ ሲሆን፣ ለተረጂዎች በመቅረብ ላይ ያለው የእህል አቅርቦት በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሊያልቅ እንደሚችል ድርጅቱ ማሳሰቡን ሮይተርስ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት የእርዳታ ፍላጎቱን ከአቅርቦቱ ጋር ሊመጣጠን አለመቻሉን የገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሊያ ክልል ያለው የምግብ አቅርቦት እጥረት አሳሳቢ መሆኑን በድጋሚ አስታውቋል።

ለተረጂዎች በየዕለቱ የምግብ አቅርቦት አለማድረጉ ችግሩን ለመቋቋም እንዲሁም ተረጂዎች ማገገም የሚፈጅባቸውን ጊዜ በሶስት እጅ እጥፍ ከፍ እንደሚያደርገው የድርጅቱ የአስቸኳይ የእርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ በዘገባው አስፍሯል።

ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ዳግም በተከሰተው የድርቅ አደጋ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ እና በደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው ይገኛሉ።

ይሁንና፣ ከተረጂዎች መካከል አብዛኞቹ ወቅታዊ ድጋፍን እያገኙ እንዳልሆነ የገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታው አቅርቦትን  ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ በትንሹ አራት ወራቶች እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።