ኢሳት (የካቲት 27 ፥ 2009)
አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ይግባኝ ለ52ኛ ጊዜ ፍርድ/ቤት የቀረቡት የዞን 9 ጦማሪያን ውሳኔ ሳያገኙ ለ53ኛ ጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ታወቀ።
ይግባኝ የተጠየቀባቸው ጦማሪያን በፍቃዱ ሃይሉ፣ ናትናዔል ፈለቀ፣ አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔ እንዲሁም ሶሊያና ሽመልስ (በሌለችበት) ተለዋጭ ቀጠሮ ለመጋቢት 11, 2009 ተሰጥቷቸዋል።
ዓቃቤ ህግ የተከሳሾቹን ከእስር መፈታት በመቃወም ያቀረበው ይግባኝ ዕልባት ሳያገኝ ለ53ኛ ጊዜ በቀጠሮ ሲሸጋገር ከጦማሪያን አንዱ በፍቃዱ ሃይሉ በግሉ በቀረበት ክስ በተመለከተ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደርጓል።
በፍቃዱ ሃይሉ ከእስር በተፈታበት ወቅት በሽብር ወንጀል የቀረበበት ክስ፣ ወደ አመጽ ማነሳሳት ዝቅ ያለለት ሲሆን፣ ሌሎች በነጻነት መፈታታቸው ይታወሳል። አቃቤ ህግ የሁሉንም በነጻ መለቀቅ በመቃወም ያቀረበው ይግባኝ በቀረበለት በአሁኑ ወቅት፣ በፈቃዱ ሃይሉ ላይ የተመሰተው የአመጽ ማነሳሳት ክስ እንዲቀጥል ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።