የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በ77 ግለሰቦች ላይ ክስ መሰረተባቸው

ኢሳት (የካቲት 27 ፥ 2009)

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆንና ነዳጅ ከጎረቤት ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ አድርገዋል የተባሉ 77 ግለሰቦች ክስ እንደተመሰረተባቸው አስታወቀ።

ከተከሳሾቹ መካከል 12ቱ ኤርትራውያን ናቸው የተባሉ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ የአርበኞች ግንቦት 7 አባል በመሆኑ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ ነበር ሲል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክሱ ማመልከቱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ተከሳሾቹ ከጥር 2 ቀን 2007 አም ጀምሮ የድርጅቱ አባል በመሆን “አደምዳሚት” በተባለ የአርበኞች ግንቦት 7 ማሰልጠኛና ሌሎች ማሰልጠኛ ቦታዎች ገብተው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመፈጸም በቡድን ተከፋፍለው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል በማለት አቃቤ ህጉ በመሰረተው ክሱ አስፍሯል።

77ቱ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በመሃል ጸገዴ፣ ከምዕራብ አርማጭሆ እስከ መተማ በታች ላይ አርማጭሆ፣ ወልቃይት መተማና ቋራ ወረዳዎች በመከፋፈል ወታደራዊ ማሰልጠኛን መመስረት እንዲሁም ነዳች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባና እስረኞችን የማስለቀቅ ተልዕኮ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም በክሱ ተመልክቷል።

በሳምንቱ መገባደጃ ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች እያንዳንዳቸው 18ሺ ብር እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ይዘው ህዳር 3 ቀን 2009 አም ከሃርና አካባቢው ተነስተው ተከዜ ወንዝን በመሻገር ህዳር 5, 2009 ዓም ኢትዮጵያ ከገቡ ብኋላ በትግራይ ቃፍታ አድርገው ሁመራ ወረዳ እንደርስ በተባለ ቦታ ህዳር 7 ቀን 2009 አም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አክሎ አስታውቋል።

ሁሉም ተከሳሾች ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች የተለያዩ ተልዕኮዎችን ሲቀበሉ ነበር ያለው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ መካከል 12 የኤርትራ ዜግነት ያላቸው መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል።

ተከሳሾቹ ክስ እንደተመሰረተባቸው ቢገለፅም የክሱ አይነት ግን በዝርዝር አልተጠቀሰም።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ አቃቤ ህግ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ  ኢሳትና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክን በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጀርባ እጃቸው አለበት በማለት ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና በዚሁ መዝገብ በዋናነት ተጠያቂ የተደረጉ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት የካቲት 30, 2009 አም ክሱን መመልከት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።