የካቲት ፳፯ ( ሃያ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጎንደር ከተማ ያለፈው ቅዳሜ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል መኖሪያ ቤት ላይ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ፣ በርካታ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ አባላት የአካባቢውን ህዝብ ሲያዋክቡ መሰንበታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። ጥቃቱ በግለሰቡ ላይ ያደረሰው ጉዳት ይኑር አይኑር የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ጥቃቱ እንደተሰማ አካባቢው በወታደሮች ታጥሮ የጥቃቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ አሰሳ ተደርጓል።በዚህም የአካባቢው ሰዎች ተይዘው እየተደበደቡ ጥቃቱን የፈጸሙትን እንዲያጋልጡ ተጠይቀዋል።
ማንነታቸውን ያልገለጹ የነጻነት ሃይሎች መሆናቸውን የጠቀሱ ቡድኖች ለኢሳት በላኩት መረጃ፣ ጥቃቱን እነሱፈጽመው ማምለጣቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ሃይሎች እንዳሉት ከንቲባው ሙሉ በሙሉ የህወሃት ታዛዥ ሆኖ የከተማውን ሃብት በወታደሮች ሲያዘርፍ ከመቆየቱም በላይ ከ370 ሺ ብር በላይ በማውጣት የመከላከያ መኮንኖችን፣ የፈዴራል ፖሊስ አባላትና የብሄራዊ መረጃ ሰራተኞችንና ሌሎችንም ሹሞች ሰብስቦ በታጋይ ጎቤ መልኬ መገደል በመደሰት በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ግብዣ አካሂዷል። የጎንደር ህዝብ በታጋይ ጎቤ መገደል ሃዘን ላይ ባለቤት በዚህ ጊዜ እንዲህ አይነት ድርጊት መፈጸም አሳዛኝ መሆኑን የጠቁሰት ሃይሎች፣ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተነግሮት ሊሰማ ባለመቻሉ አሁንም የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ይሆነው ዘንድ ይህ ድርጊት ተፈጽሞበታል ብለዋል።
በሌላ በኩል የካቲት 25 ቀን 2009 ዓም በጎንደር ከተማ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ የአርበኞች ግንቦት7 ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ገብተዋል በሚል ፍተሻ ሲያደርጉ እንደነበር፣ ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ አውቶፓርኮ በሚባለው ስፍራ ላይ ታጣቂዎች ከወታደሮች ጋር የተኩስ ለውውጥ አድርገው በሰላም ወደ ስፍራቸው መመለሳቸውን ይሁን እንጅ በተኩሱ የተደናገጠ አንድ የባጃጅ አሽከርካሪ ከፒክ አፕ መኪና ጋር በመጋጨቱ በሰዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ለኢሳት በላኩት መረጃ ገልጸዋል።
በዚሁ ጥቃት የተደናገጠው አገዛዙ ከ400 ያላነሱ ወታደሮችን አስገብቶ አሰሳ እያደረገ መሆኑን በተለይም በቀበሌ 18 ጂቲዜድ ሰፈር፣ ሽንታ ወንዝና ዳብርቃ በሚባለው አካባቢው ቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ በርካታ ሰዎችን እየደበደቡ ማሰራቸውን ፣ ያም ሆኖ አንድም ታጋይ አለመያዙን በላኩት መረጃ አስታውቀዋል።
መረጃውን በማስመልከት ለጎንደር ከተማ መስተዳደር ጽ/ቤት ስልክ ብንደውልም መልስ የሚሰጠን አካል አላገኘንም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ነገ 6ኛ ወሩን ቢይዝም፣ አዋጁን ለማንሳት ምንም አይነት ፍንጭ አለመኖሩን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል።