የካቲት ፳፯ ( ሃያ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ሦስት የሙስሊም አባቶች ካለፈው አርብ ጀምሮ እስካሁን ምክንያቱ ባልተገለጸላቸው ሁኔታ በጂንካ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ምንጮች ገለጹ፡፡ አባቶችን ለመያዝ በዞኑ ኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ ቤታቸውን የፈተሸው ቡድን ከሃይማኖታዊ ስነስርዓት ውጭ በሆነ ሁኔታ መስገጃቸውን በጫማቸው በመርገጥ ፣ የህጻናት የመማሪያ ደብተሮች ሳይቀር በማገላበጥና የቤት ዕቃዎችን በመበታተን ፍተሻ ያደረጉ ሲሆን፣ ከየቤታቸው ያገኙዋቸውን የሃማኖት መጻህፍት በሙሉ ወስደዋል። ፍተሻውን ያከናወኑበት መንገድ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ጎሬቤቶቻቸውንና ሁኔታውን የተመለከቱትን የከተማው ነዋሪዎች በሙሉ አበሳጭቷል።
በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር የዋሉት አባቶች የዞኑ ሸሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ አብዱል ማልክ ኢብሪሂም፣ የጂንካ ከተማ እስልምና ጉዳይ ሰብሳቢ ናስር አሊ እና የሃይማኖት መምህርና የሁለተኛ ደረጃ መምህር፣ ኡስታዝ ዱባለ ደምሴ ናቸው።
ከዓመታት በፊት መንግስት በህዝቡ ላይ ለመጫን የሞከረውን የአህባሽ አስተምህሮ ተከትሎ በዞኑ ሙስሊሞች መካከል ልዩነት መፈጠሩንና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመንግስት የሚደገፈው ቡድን የሙስሊም አመራሮቹን አሳስሮ የዞኑ የእስልምና ጉዳዮችን አመራር ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት የሙስሊም ማኅበረሰቡ ከታሳሪዎች ጎን በአንድነት በመቆሙ ከሽፎበት እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።
የስልጣን ይገባኛል ጥያቄው በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ወደ ፍርድ ቤት ተወስዶ ትክክለኛው አመራር አሁን የታሰሩት እንደሆኑ ውሳኔ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሸነፈው የመንግስት ተደጋፊ ቡድን ‹‹ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የማያውቀውና የማይቀበለው ህገወጥ ማኅተም›› በማስቀረጽ፣ በዞኑ ሁለት የሙስሊም አመራር እንዳለ በሚያስመስል መልክ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ፣ አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መከታና ተገን በማድረግ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሰፊ ተቀባይነት እና ህጋዊ ውክልና ያለውን አመራር ለማስፈራራትና ሥልጣኑን ለመውሰድ ያደረገው ሁለተኛ ዙር ሴራ መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
እስከ ቅዳሜ ከሰዓት ድረስ ታሳሪዎቹን ማንም እንዳላነጋገራቸው፣ቃላቸውን እንዲሰጡ እንዳልተደረገና የታሰሩበት የተጠረጠሩበት ምክንያትም እንዳልተገለጸላቸው ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡