ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል በፈጸሙት ጥቃት ከሶስት ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅቱ አስታወቀ።
በኦጃሎ በኦትዎል እና አጎራባቸው ባሉ ቀበሌዎች ካለፈው ወር ጀምሮ በተፈጸሙ የድንበር ዘለል ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች መኖሩን ቢያረገግጥም ቁጥራቸው ከመግለጽ ድርጅቱ ተቆጥቧል።
ከቀያቸው የተፈናቀሉ 3ሺ 714 ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት በአንጎይ ከተማ እንዲሁም በአለሚና ቶ’ኦ ቀበሌዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ታውቋል።
በአካባቢው የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያ ባለሙያዎችን በማሰማራት ለተፈናቃዮች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ላይ ጥናት ማካሄዱን አመልክቷል።
በአጎራባች ቀበሌዎች ተጠልለው ለሚገኙ ለነዚሁ ነዋሪዎች የአስቸኳይ የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎች እንደሚያስፈልጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪውን አቅርቧል።
በክልሉ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በአካባቢው የጸጥታ አባላትን አሰማርቶ ኣንደሚገኝም ተመልክቷል።
ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ከደቡብ ሱዳን ሰርገው የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወደ 140 አካባቢ ሰዎች መገደላቸውና ከ100 የሚበልጡ ህጻናት ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸው ይታወሳል።
መንግስት በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል በተካሄድው ድርድር የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከታገቱ አብዛኛው ህጻናትን ለቀው እንደነበር ተመድ የህጻናትን መርጃ ድርጅቱ (ዩኒሴፍ) ሲገልጽ ቆይቷል።
ተመሳሳይ ጥቃቱ ካለፈው ወር ጀምሮ መፈጸሙን ያስታወቀው ተመድ፣ ጥቃቱ በአካባቢው በተያዘው ወር የሚጠበቀው ዝናብ መጣል እስኪጀምር ድረስ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል አክሎ አስታውቋል።
የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ቀበሌዎች ስለደረሰው የነዋሪዎች ሞትና መፈናቀል እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።