በአውሮፓ ህብረት በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ ጉዳይ አለመካተቱ ቅሬታ እንዳሳደረበት አንድ ተቋም ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2009)

የአውሮፓ ህብረት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በተያዘው የፈረንጆች 2017 አም በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረትን እንዲያገኙ ያወጣውን አጀንዳ የኢትዮጵያ ጉዳይን አለማካተቱ ስጋት እንዳሳደረበት አንድ አለም አቀፍ ተቋም ገለጸ።

መቀመጫውን በኔዘርላንድ ቤልጅየም ያደረገው Unrepresented Nations and People’s Organization የተሰኘው ይኸው ተቋም በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መት ሁኔታ ከመቼው ጊዜ በላይ አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል።

ይሁንና የሃገሪቱ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ችግር የአውሮፓ ህብረት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትኩረት እንዲያገኙ ባቀረበው አጀንዳ አለመካተቱ ስጋት አሳድሮብኛል ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።

የአውሮፓ ህብረት በተያዘው የፈረንጆች 2017 አም በአለም ዙሪያ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኩል ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ ያላቸው አጀንዳዎች በባለ 10 ገፅ ሪፖርቱ የዘረዘረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ አለመካተቱን ከሪፖርቱም መረዳት ተችሏል።

ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ግድያ የተፈጸመባቸው ሰዎች ድርጊት በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት የአውሮፓ ህብረት ጥያቄን ሲይቀረብ መቆየቱ ይታወሳል።

የአውሮፓ ፓርላማ ህብረቱ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ ጠንካራ ዕርምጃን እንዲወስድ ጥያቄን ሲያቀርብ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ፈጽሞታል ያለውን ግድያና አፈና የኮነነው የአውሮፓ ህብረት በተያዘው አመት የሰብዓዊ መብት መከበር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በሪፖርቱ አስቀምጧል።

ይኸው የህብረቱ የዘንድሮ አጀንዳ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ረገጣና አፈርን ችላ ማለት የሌለበት  ጉዳይ እንደሆነ በሰብዊ መብቶች መከበር ዙሪያ በአለም ዙሪያ የሚሰራው ተቋም አመልክቷል።

ድርጅቱ ባቀረበው ዙሪያ ህብረቱ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።

ህብረቱ ሲገልጽ የቆየውን ይህንኑ ስጋት ተከትሎ የተለያዩ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ከሚያደርጉት ጉዞ እንዲታቀቡ ሲያሳስቡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

የብሪታኒያ መንግስት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በማድረግ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ስታስጠነቅቅ የቆየች ሲሆን፣ የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለይ በአማራ ክልል በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች ውጥረት መኖሩን በአዲስ መልክ ባሰፈረው የጉዞ ማሳሰቢያው ዳግም አመልክቷል።