ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2009)
በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘው የኬንያ መከላከያ ሰራዊት ከአል-ሸባብ ታጣቂ ሃይል ጋር ባካሄደው ውጊያ በትንሹ 57 ታጣቂዎችን መግደሉን አስታወቀ።
በታችኛው ጁባ የደቡባዊ ሶማሊያ ግዛት ተካሄዷል በተባለው በዚሁ የሁለቱ ወገኖች ፍልሚያ የጦር ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ የተለያዩ ከባድ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለው እንደነበር የኬንያ መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጆሴፍ አውቱ ለጋዜጠኞች መግለጻቸውን ዘ-ስታንዳድር የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ሃጋን እና አፍማዶ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ለሰዓታት ተካሄዷል በተባለው በዚሁ ውጊያ በግጭቱ ከሞቱት ታጣቂዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ የአልሸባብ ተዋጊዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ወታደራዊ ሃላፊው አስታውቀዋል።
የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል በአካባቢው ይንቀሳቀስ በነበረ ወታደራዊ ተሽከርካሪ የፈጸመውን የደፈጣ ጥቃት ተከትሎ በሁለቱ ወገኖች መካከል ከባድ ጦርነት መካሄዱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለመገኛኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ በጥቃቱ ዙሪያ የሰጠው ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የሌለ ሲሆን፣ የኬንያ መከላከያ ሰራዊት ከግጭቱ ያመለጡ ታጣቂዎች በማደን ላይ እንደሚገኝ አክሎ ገልጿል።
ባለፉት ጥቂት ወራቶች አልሸባብ በኬንያ ወታደሮች ላይ ተከታታይ ጥቃት ሲፈጸም መቆየቱ አይዘነጋም።
የሶማሌያ የጸጥታ ስጋት ነው የሚባለው አልሸባብ በኬንያ ወታደሮች ላይ በተለያዩ ጊዜያት በፈጸመው ጥቃት ከ100 የሚበልጡ የኬንያ ወታደሮች መገደላቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2011 አም ጀምሮ ሰራዊቷን በሶማሊያ አሰማርታ የምትገኘው ኬንያ በአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ላይ እንዲህ ያለ ወታደራዊ ጥቃት ስታደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
ሃገሪቱ በሺዎች የሚቆጣሩ ወታደሮቿን በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር አሰማርታ የምትገኝ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ማላዊ፣ ብሩንዲና፣ ጅቡቲ የተውጣጡ ወደ 22 ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪዎች በሶማሊያ እንደሚገኙ የሰላም አስከባሪ ሃይሉ መረጃ ያመለክታል።
ይሁንና አልሸባብ አሁንም ድረስ የሶማሊያ የጸጥታ ስጋት ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ አለም አቀፍ አካላት በሃገሪቱ ተሰማርቶ የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ሃይል የተጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳላመጣ ይገልጻሉ።
የሰላም አስከባሪ ሃይሉ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ውስጥ ከሃገሪቱ ለቆ እንደሚወጣ በማስታወቅ ላይ ሲሆን፣ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ላይ ሰራዊት በማሰማራት አዲስ ጥቃት ሊካሄድ እንደሚችል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የኬንያ ወታደሮች ከታጣቂ ሃይሉ ጋር ባካሄዱት ጦርነት በሃገሪቱ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ተሳታፊ እንደነበሩም ለመረዳት ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ወደ 50 የሚጠጉ ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታ የምትገኝ ሲሆን፣ ወታደሮቹ በስለላ የመረጃ አገልግሎትና በስልጠና ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ተመልክቷል።
ይሁንና አሜሪካ የወታደሮቿን ቁጥር ከፍ በማድረግ በታጣቂ ሃይሉ ላይ አዲስ የጥቃት እቅድ መደገፏ ባለፈው ሳምንት መገለጹ ይታወሳል።