በሶማሊ እና በኦሮምያ ክልሎች ድንበር አካባቢ የሚታየው ውጥረት መቀጠሉን ተከትሎ ነዋሪዎች እየሸሹ ነው

የካቲት ፳፬ ( ሃያ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት የሶማሊ ልዩ ሚሊሺያ ወደ ኦሮምያ ክልል በመግባት በህዝብ ላይ በቀጥታ በመተኮስ ከፍተኛ አደጋ ያስከተለ ሲሆን፣ በምስራቅ ሃረርጌ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የሶማሊ ክልል አርማን እያውለበለቡ መሬቱ የእነሱ እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ከልዩ ሃይሉ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመቋቋም የሞከሩ የኦሮምያ ክልል ነዋሪዎች ፣ ልዩ ሃይሉ ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በመተባበር የሚፈጽመውን ጥቃት መቋቋም እንዳልቻሉ ይገልጻሉ። ሁኔታው አስከፊ በመሆኑም በአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎች እየተሰደዱ ነው።
የሶማሊ ክልል ልዩ ሃይል አባላት በተለይ ጭናክሰን፣ ባቢሌ፣ ጉርሱም እና አዋሳኝ ቦታዎችን የጥቃታቸው ኢላማ ማድረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በግጭቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን አስታውቆ ነበር።