የካቲት ፳፬ ( ሃያ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ወሎ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የነበረው አቶ መኳንንት ካሳሁን ከሃሙስ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከስራ ቦታው በደኅንነቶች ታፍኖ ከተወሰደበት ጊዜ አንስቶ እስከዛሬ ያለበት አድራሻ ባለመታወቁ ወላጅ እናቱን ጨምሮ መላው ቤተሰቡ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መውደቃቸውን ለኢሳት ተናግረዋል።
ደሴ ከተማ ውስጥ የሚኖረው አቶ መኳንንት ከስራ ቦታው ስፖርት ቤት ውስጥ ታርጋ በሌለው መኪና ተጭነው የመጡ ስድስት ታጣቂዎች አብረውት የነበሩትን በመሳሪያ አስፈራተው አስገዳጅ ሃይል በመጠቀም አፍነው ወስደውታል።
የፓሊስ ጣቢያዎችን፣ እስር ቤቶችን እና የብአዴን ጽ/ቤትን ጨምሮ ይመለከታቸዋል ወደሚሏቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ልጃቸውን ፍለጋ የተንከራተቱት ወላጅ እናቱ፣ ላለፉት 11 ቀናት ቢደክሙም የልጃቸውን አድራሻ ማወቅ እንዳልቻሉና ድጋሜም ልጃቸውን ፍለጋ እንዳይመጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ ሲሉም የተማጽኖ ጥሪያቸውን አሰምተዋል።
የአቶ መኳንንት ካሳሁንን አድራሻ መጥፋትን አስመልክቶ በሰማያዊ ፓርቲ በኩል እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አለመሰጠቱ እንዳሳዘናቸው ወላጅ እናቱ አክለው አስረድተዋል።