የካቲት ፳፬ ( ሃያ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ዓመት ለበርካታ ዜጎች ሞት ምክንያት የነበረው የኮሌራ ወረርሽኝ በድጋሜ በባህር ዳር አካባቢ አንዳሳ ቀበሌ መከሰቱን ከጤና ጥበቃ ቢሮ የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
በበሽታው ከሰላሳ በላይ ሰዎች መለከፋቸውን የሚጠቁመው መረጃ ፣ ታማሚዎችን በባህርዳር ከተማ አዲስ በመሰራት ላይ ባለው ሆስፒታል ለማከም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡በሽታው በቀጣዩ የዝናብ ወቅት ሊቀጥል እንደሚችል የተናገሩት ባለሙያዎች ከአሁን በፊት በሽታው በታየባቸው አካባቢዎች እንደገና ያገረሻል የሚል ስጋት አላቸው፡፡
በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ ህዝብን እየገደለ ያለው ይሄው የኮሌራ በሽታን ለመቋቋም የሶማሌ ክልል ባለመቻሉ ከአማራና መሰል ክልሎች የባለሙያ ትብብር በመጠየቅ ላይ ነው፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በዳባት ወረዳ ለኩፍኝ ተብሎ የተሰጠው ክትባት፣ አንድ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ የገደለ ሲሆን በርካቶች መታመማቸውን ከአካበቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡