121ኛው የአድዋ ድል በአል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2009)

ኢትዮጵያውያን ከ100 አመት በፊት ወራሪው የኢጣሊያ ጦርን በአድዋ ድል ያደረጉት 121ኛው የአድዋ ድል በአል ሃሙስ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።

የበአሉ አከባበር በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው በዳግማዊ ሚኒሊክ አደባባይ አባት አርበኞች፣ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ሃገራት ተወካዮች በተገኙበት መከበሩ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

በዚሁ አመታዊ በዓል አከባበር ላይ የታደሙ አባት አርበኞች የአሁኑ ትውልድ የወረሰውን የአድዋ ድል ለቀጣዩ ትውልድ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ የማስተላለፍ ታላቅ ሃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።

ይኸው የድል በዓል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ድል መሆኑን የተናገሩት አርበኞቹ የአሁኑ ትውልድ የአድዋል ድል በዓል አከባበርን የራሱ አሻራን ለማስቀረት ሊጠቀምበት እንደነበርም አክለው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተከበረው ዝግጅት በተጨማሪ 121ኛው የአድዋ ድል በዓል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት በአድዋ ድሉ በተከበረበት ስፍራም መከበሩ ታውቋል።

የአድዋ ድል በዓል አከባበርን በተመለከተ ከኢትዮጵያን በተጨማሪ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የታሪክና ምሁራንና ሌሎች አካላት በአሉ የአፍሪካውያን ድል ጭምር መሆኑን በማውሳት በተለያዩ የማህበራዊ ድረገጾች መልዕክትን አስተላልፈዋል።

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ የአድዋ ድል ለአፍሪካ ያለው ታሪካዊነት ትርጉምና ትስስር በማስመልከት ለአፍሪካውያን መልዕክታቸውን አቅርበዋል።

በተለያዩ የአለማችን ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የበአሉ አከባበርን በተለያዩ ዝግጅቶች በመዘከር ላይ መሆናቸውንም ለመረዳት ተችሏል።