ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2009)
በመገንባት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ላይ ጥቃትን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ የቤኒሻንጉል ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) 13 ታጣቂዎች መገደላቸውን መንግስት ገለጸ።
በተወስደባቸው ዕርምጃ ከተገደሉት ታጣቂዎች በተጨማሪ ሰባቱ ወደ ጎረቤት ሱዳን ከሸሹ በኋላ ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውንና የንቅናቄው አባላት መነሻቸውን ከኤርትራ እንዳደረጉ የመንግስት ቃል አቀባይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘዲግ አብርሃን ዋቢ በማድረግ አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ይሁንና የኤርትራ መንግስት ጥቃት ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ሰለተባለው አማጺ ቡድን የሚያወቀው ነገር እንደሌለ ማስተባበያ መሰጠቱን ብሉምበርግ የዜና አውታር ሃሙስ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አስነብቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ ያቀረበው ውንጀላ (ክስ) ትርጉም የሌለውና ትኩረትን አልያም ሌላ መልዕክትን ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑን የሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር የስጡትን ምላሽ በመጥቀስ ብሉምበርግ አመልክቷል።
አቶ ዛድግ አብርሃ በበኩላቸው ዕርምጃ የተወሰደባቸውና በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉት የንቅናቄው አባላት በኤርትራ መንግስት በግልፅ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑ ታውቋል ሲሉ ለአሶሼይትድ ፕሬስ አስታውቀዋል።
የሱዳን መንግስት አሳልፎ ሰጥቷል ስለተባለው የንቅናቄ አባላት በተመለከተ ብሉምበርግ የዜና አውታር ከሃገሪቱ መንግስት ማረጋገጫ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ምላሽ ሊያገኘ አለመቻሉን በዘገባው አስፍሯል።
ጥቃት ሊፈጸም ነበር የተባለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄም እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው ማስተባበያ ሆነ ምላሽ የለም።
መንግስት ታጣቂዎቹን ወደ ግድቡ በማቅናት ላይ ነበሩ ቢልም ዕርምጃው የተወሰደበትን ስፍራ በትክክል አላመለከተም።