ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ያደረጉት ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ሲል የሱዳን አማጺ ቡድን አስታወቀ

ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2009)

ኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስት ሰሞኑን ያደረጉት ሰምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን ውስጥ በአባልነት የሚገኝ አንድ አንጃ ገለጸ።

የኑዌር ጎሳዎች በአብዛኛው እንደሚወክል የሚነገርለት የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ተቃውሞ አንጃ በደቡብ ሱዳን ሰላም በሌለበት ሁኔታ ሁለቱ ሃገራት የደረሱት ስምምነት ተፈጻሚ እንደማይሆን የአንጃው አመራሮች መግለጻቸውን ራዲዮ ታማዙጂ የተሰኘ ጣቢያ ዘግቧል።

የአንጃው ምክትል ወታደራዊ ቃል አቀባይ የሆኑት ዲክሰን ጋትሉአክ ከሪክ ማቻር አማጺ ቡድን ታማኝ የሆነው አንጃው ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋሰኑ ሰፊ ግዛቶችን ተቆጣጥቶ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የፕሬዚደንት ሳልባኪር መንግስት አንጃው እንዲሁም ሌሎች አካላትን ያሳተፈ ባለመሆኑ ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም ሲሉ ለራዲዮ ጣቢያው አስረድተዋል። ባለፈው ሳምንት ሁለቱ ሃገራት በድንበር ዙሪያ ያሉ የጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ አንደኛው ሃገር የሌላኛውን ሃገር አማጺ ቡዳን እንደማይደግፍ ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል። ይሁንና ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተፈራረሙት ይኸው ስምምነት በሪክ ማቻር የሚመራውን አማጺ ቡድንም ሆነ ሌሎች አንጃዎች ያካተተ ባለመሆኑ ስምምነቱ በነዚሁ አካላት ዘንድ ጥርጣሬ ማሳደሩ ተመልክቷል።

ሁለቱ ሃገራት የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ምላሽን የሰጠው የሪክ ማቻር አማጺ ቡዳን አንጃ በደቡብ ሱዳን አስተማማማኝ እና ሁሉን ያሳተፈ ድርድር ካልተካሄድ ኢትዮጵያና የፕሬዚደንት ሳል ባኪር መንግስት በየጊዜው የሚያደርጉት ስምምነት ተግባራዊ እንደማይሆን አስታውቋል።

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉ አካላት በበኩላቸው ሁለቱ ሃገራት አንደኛውን ሃገር አማጺ ላለመደገፍ ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት ስምምነት በሌሎች አማጺያንንና አንጃዎች መካከል ተቀባይነት እና ድጋፍ አለማግኘቱ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ከወራት በፊት ከደቡብ ሱዳን ጋር የደረሰችውን ተመሳሳይ ስምምነት ተከትሎ ከአንድ አመት በላይ በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን አድርገው የነበሩት ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንደማይገቡ እገዳ መጣሏ ይታወሳል።

የሪክ ማቻር አማጺ ቡድን አመራሮች ኢትዮጵያ የወሰደችው ዕርምጃ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሁለቱ ወገኖች መካከል የተቋረጠው ስምምነት ቀጣይ በሚሆንበት ጉዳይ ዙሪያ የሚመክር የልዑካን ቡድን ባለፈው ወር ወደ ጁባ ልኮ እንደነበረም አይዘነጋም። ለሪክ ማቻር ከለላን ሰጥታ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ ሁለቱ ወገኖች ፊት ለፊት ተገናኘተው እንዲወያዩ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗ ታውቋል።