ኢሳት (የካቲት 22 ፥ 2009)
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ወደ 500ሺ አካባቢ የሚጠጉ የኤርትራና የሶማሊያ ስደተኞች በሱዳን እንደሚገኙ የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ።
ሰሞኑን ሱዳን በኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ ፈጽማዋለች የተባለውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ተከትሎ ለሃገሪቱ የሚሰጠውን የስደተኞች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቋርጥ የተጠየቀው ህብረቱ ለሃገሪቱ እስካሁን ድረስ የለቀቀው ድጋፍ አለመኖሩን ገልጿል።
የሱዳን የድንበር ተቆጣጣሪ ሃይሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ወደ ሃገሪቱ ድንበርን እያቋረጡ የሚገቡ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ማስታወቁ ይታወሳል።
በሃገሪቱ በሚገኙ የጎረቤት ሃገራት ስደተኞች ዙሪያ ሪፖርትን ያወጣው የአውሮፓ ህብረት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የኤርትራና የሶማሌ ስደተኞች በሱዳን እንደሚገኙ ማመልከቱን ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።
እነዚሁ ስደተኞች ሃገሪቱን መሸጋገሪያ በማድረግ ወደ አውሮፓ የመግባት እቅድ እንዳላቸው ተነግሯል።
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 አም ብቻ ወደ 30ሺ የሚጠጉ ስደተኞች ከሱዳን ወደ ጣሊያን ያቀኑ ሲሆን፣ ድርጊቱ ስጋት ያሳደረበት የአውሮፓ ህብረት ሃገሪቱ የስደተኞች ቁጥጥሯን እንድታጠናክር በሚል የ100 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ በቅርቡ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ይሁንና፣ የሱዳን መንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቅርቡ በኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ፈጽመውታል የተባለ ድብደባና እስራት ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ ህብረቱ ለሃገሪቱ ሊሰጥ ያቀደውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቋርጥ ጥያቄን አቅርቦ ይገኛል።
ለዚሁ ጥያቄ ምላሽን የሰጠው የአውሮፓ ህብረት እስከአሁን ድረስ ሃገሪቱ የተለቀቀ የገንዘብ ድጋፍ እንደሌለና ልገሳው በአለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ተግባራዊ የሚደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሱዳን መንግስት በመኖሪያ ፈቃድ ክፍያ ላይ ያደረገውን የክፍያ ጭማሪ እንዲያጤነው ኢትዮጵያውያኑ ኤምባሲው ጥረት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይሁንና ኢትዮጵያውያኑ ጥያቄያቸውን ባቀረቡ ጊዜ የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ከኤምባሲው የቀረበላቸው ጥሪ ተከትሎ ሰላማዊ ሰልፉን ለመበተን በወሰዱት ዕርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩት ለእስር መዳረጋቸው ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።
ለእስር ከተዳረጉት መካከል 65 አካባቢ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በ40 የጅራፍ ግርፋት እንዲቀጡ መደረጉም ሲዘገብ ቆይቷል። የመረጃውን መውጣት ተከትሎም የአውሮፓ ፓርላማ ሱዳን በስደተኞቹ ላይ ፈጽማዋለች ያለውን ድርጊት በጽኑ ኮንኗል።
በርካታ የህብረቱ የፓርላማ አባላት የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች የፈጸሙት ድብደባና እስራት አስቸኳይ ማጣራት እንዲካሄድበት ጥያቄን ያቀረቡ የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች የፈጸሙት ድብደባና እስራት አስቸኳይ ማጣራት እንዲካሄድበት ጥያቄን ያቀረቡ ሲሆን፣ የሱዳን መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው ምላሽ የለም።
የአውሮፓ ህብረት ለእስር በተዳረጉና ታስረው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ማጣራት እንዲካሄድበት ጥያቄን ቢያቀርብም፣ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ድረስ የገለጸው ነገር የለም።