በአዲስ አበባ አንድ ጣሊያናዊን የገደሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ ነው ተባለ

ኢሳት (የካቲት 22 ፥ 2009)

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በጥይት የተገደለ ጣሊያናዊ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ስሙ ያልተገለጸው የ32 አመት ጣሊያናዊ የካቲት 18 ምሽት በከተማዋ ቦሌ ክፍለ ከተማ በአንድ የምሽት ክበብ በመዝናናት ላይ እንዳለ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ ማለፉን በስፍራው የነበሩ እማኞች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ተቋማት አስረድተዋል።

ሟች ከጓደኞቹ ጋር በመዝናናት ላይ እንዳለ ስልክ ተደውሎለት ወደ ውጭ ለማነጋገር በወጣበት ወቅት በአንድ ተሽከርካሪ ውስጥ ከነበሩና ከማይታወቁ ሰዎች በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ መውደቁን እንደሰማ ፖሊስ አረጋግጧል።

ይሁንና ፖሊስ ግድያውን ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ለቀናት የዘለቀ ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። ግድያ የተፈጸመበት ጣሊያናዊ ከአምስት አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከቤተሰቦቹ ጋር በመኖር ላይ እንደነበረም ለመረዳት ተችሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግድያው በተፈጸመበት ወቅት አብረው የነበሩ ቁጥራቸው ያልተወቁ ገለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ የነበረ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ ይለቀቁ አይለቀቁ የተገለጸ ነገር የለም።

የሟች ወንድም የሆኑት አቶ ሳቬሪዬ ጉለን ወንድማቸው በኢትዮጵያ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከማንም ጋር ምንም አይነት ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደማያውቅና ድርጊቱ በቤተሰባቸው ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሮ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ታናሽ ወንድማቸው የቀብር ሰነስርዓቱ የካቲት 21 ቀን 2009 አም በአዲስ አበበ ከተማ በሚገኘው የካቶሊካዊያን መካነ መቃብር መፈጸሙን ተናግረዋል።

በከተማዋ በተኩስ ጥይት የሚፈጸሙ ወንጀሎች የተለመዱ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።