ኢሳት (የካቲት 22 ፥ 2009)
በአማራ ክልል ከተቀጣጠለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወዲህ በከፍተኛ ልዩ ጥበቃ ውስጥ የሚገኙ የጎንደርና የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች በኮማንድ ፖስቱ ተጨማሪ ተጽዕኖ እየተደረገባቸው መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ። በዚሁም የባህርዳር ከነማና የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ዝርዝር ለኮማንድ ፖስቱ መመሪያ ተላልፏል። በሌላ በኩል በወህኒ ቤት የሚገኙ እስረኞችን በአማራ ክልል ቴሌቪዥን መቅረጽ ተጀምሯል።
በሃምሌ 2008 ዓም መጀመሪያ በጎንደር የተነሳውና ወደ ባህርዳርም የተሻገረው ህዝባዊ ተቃውሞ በከፍተኛ የሃይል ዕርምጃ መዳከሙን ተከትሎ፣ ህዝቡ ብሶቱንና ተቃውሞን በእግር ኳስ ሜዳዎች መግለጹን ቀጥሏል። ለህዝብ መሰባሰብና ለተቃውሞው ምክንያት ናቸው ተብለው የተወሰዱት የጎንደር ፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድንና፣ የባህርዳሩ ባህርዳር ከነማ በመሆናቸው የደጋፊዎቹ ዝርዝር ለኮማንድ ፖስቱ እንዲሰጥ መመሪያ ተላልፏል።
ሁለቱም ቡድኖች በይፋ የሚታወቅ የተመዘገቡ ደጋፊዎች እንዳሏቸው መረዳት የተቻለ ሲሆን፣ ሜዳ ውስጥ ገብተው ኳስ ከሚመለከቱት በደጋፊነት የተመዘገቡት ጥቂት መሆናቸው ተመልክቷል። ኮምናድ ፖስቱ ያልተመዘገቡትን እንዴት እንደሚቆጣጠር ግልጽ አልሆነም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ በአማራ ክልል በጎንደርና ባህርዳር ወህኒ ቤት ውስጥ የሚገኙ እስረኞችን የአማራ ክልል ቴሌቪዥን በመቅረጽ ላይ መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል። ቀረጻው የሚካሄደው መንግስት ሲወጉ በቁጥጥር ስር የዋሉ በሚል ሲሆን፣ በየትኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ ያልነበሩ፣ ግለሰቦችም አማጺያን ናቸው በማለት ቀረጻ ላይ መሆናቸው ለመረዳት ተችሏል።
ከቀረጻው በፊት ለተወሰኑት ምን እንደሚናገሩ ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን፣ ከኤርትራ መንግስት እንዲሁም ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ (ኢድሃን) ጋር ግንኙነት አለን በሚል መግለጫ እንዲሰጡ በተነገራቸው መሰረት ተግባራዊ ማድረጋቸው ተገልጿል።