ታጋይ ጎቤ መልኬ መስዋቱ ታወቀ

የካቲት ፳፪ ( ሃያ ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የነጻነት አርበኛው ታጋይ ጎቤ መልኬ ከሃምሌ 5 ቀን 2008 ዓም ጀምሮ የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝን በመሳሪያ ሲፋለም ቆይቶ፣ መሰዋቱን ምንጮች ገልጸዋል። በጀግንነቱ የብዙ ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ የገዛው የ70 አመቱ ታጋይ ጎቤ፣ በእሱ የሚመራው ሃይል ከህዳር 16 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ በገዢው ፓርቲ ወታደሮች ላይ በተዳጋጋሚ ሲያደርስ በነበረው ጥቃት ከፍተኛ ዝናን አትርፏል።
የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ እንዲከበር በሰላማዊ መንገድ ጥረት ሲያደርግ ከቆየ በሁዋላ ፣ አገዛዙ በኮ/ል ደመቀ ዘውዴና በሌሎችም የኮሚቴው አባላት ላይ የወሰደውን እርምጃ በመቃወም ፣ አገዛዙን በሃይል ለመፋለም መወሰኑን በአንድ ወቅት ለኢሳት በሰጠው ቃለምልልስ አስታውቆ ነበር። የታጋይ ጎቤ በረሃ መግባትና የሚሰነዝራቸው ጥቃቶች ያስደነገጠው አገዛዙ፣ በታጋዩ ቤተሰቦችና ዘመዶች ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ቆይቷል። የታጋዩን ከፍተኛ የሆነ ህብትና ንብረት በመዝረፍም ለመበቀል ሞክሯል። ታጋይ አርበኛ ጎቤ ስለተወሰደበት ሃብትና ንብረት ተጠይቆ ፣ “ ነጻነት ሳይኖር ሃብት ምን ይፈይዳል” የሚል መልስ ሰጥቶ ነበር።
የታጋይ ጎቤ አሟሟትን በተመለከተ የተለያዩ ወሬዎች እየተሰራጩ ሲሆን፣ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ ግን ታጋይ ጎቤ በጦርነት አልተገደለም። ይሁን እንጅ አገዛዙ አርበኛውን በጦርነት እንደገደለው አድርጎ ለማቅርብ እየተሯሯጠ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። ከተጋይ ጎቤ ጋር የተሰለፉ ታጋዮች የመሪያቸውን መስዋትነት እንደሰሙ ሌሊቱን ጥቃት ፈጽመው የበቀል እርምጃ መውሰዳቸውንና ዛሬም በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ሰፍኖ መዋሉን ምንጮች አክለው ተናግረዋል ።
የታጋይ ጎቤን መሰዋት መሆን በተመለከተ የጎንደር ህብረት ባወጣው መግለጫ “በሀገር ፍቅር አቻ የለሹ ጎቤ ምንም ያልጎደለዉ ባለፀጋ ለራሱ ምንም የማይፈልግ ነበር። ነገር ግን ወያኔ በህዝብ ላይ የሚደርሰዉን መከራና ግፍ በመቃወም ከፊት ቀድሞ የትግሉ መሪ በመሆን በረሀ በመግባት ለለፉት ስምንት ወራት በጽናት እና በጄግንነት ሲፋለም መቆየቱ ይታወቃል።ጄግናው ጎቤ በተለያዩ ቀናት ብዙ አዉደ ወጊያውችንም በማካሄድ አያሌ የጠላት ሀይልን የደመሰሰ እና እንኳን አውደ ውጊያው ስሙ የወያኔን መንደር ሲያርድ ሲያርበደብድ ወራቶችን አስቆጥሯል። የወንዶች ቁና ጎቤ በአንድ አውደ ውጊያ የመቁሰል አደጋ ደርሶበት ከወገን በተደረገለት ልዩ ድጋፍ ከቁስሉ አገግሞ በበለጠ ትግሉን ለማጠናከር በትልቅ ጽናት ዝግጅት ላይ እንዳለ ባልታሰበ ቀን፣ ባሳደገው፣ ምንም ባልጠረጠረው ለጠላት ወያኔ በጥቅም በተገዛ፣ በራሱ በቅርብ የቤተሰቡ አባል ይህ የወገን መመኪያ ጄግና የተሰዋ ሲሆን ፣ ገዳዮም በወያኔ ሔሊኮፕተር ግድያውን እንደፈፀመ ወዲያውኑ ወደ ጎንድር እንደተወሰደ ከስፍራው መረጃወች ደርሰዉናል።” ብሎአል።