የካቲት ፳፪ ( ሃያ ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው እሁድ የካቲት 19፣ 2009 ዓም አርባምንጭ ከተማ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በአርባምንጭ ከነማ ቡድኖች መካከል የተደረገውን የእግር ኳስ ጨዋታ ተከትሎ፣ በፖሊስና በህዝብ መካከል በተፈጠረው ግጭት 2 ህጻናትና አንድ ጎልማሳ ተገድለዋል። የአይን እማኖች እንዳሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባማንጭን 4 ለ1 እየመራ በነበረበት ወቅት፣ በመጨረሻው ሰአት ላይ አንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ፣ ኳስ ሲያቀብል የነበረን ወጣት በእርግጫ በመማታቱ አንዳንድ የስታዲየሙ ተመልካቾች በንዴት ድንጋይ በመወርወር ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶች የስታዲየሙን ሁለቱንም በሮች በመዝጋትና ሰዎች እንዳይወጡ በመከልከል፣ ተመልካቹን በዱላ ደብድበዋል። ህዝቡ የስታዲየሙን አጥር እየሰበረ በመውጣት ከድብደባ ለማምለጥ ሲሞክር የአስለቃሽ ጪስ የተተኮሰበት ሲሆን፣ ራሳቸውን ለማዳን ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ቢገባም አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ያስወጡት ሲሆን፣ ህዝቡ ወደ ማረሚያ ቤት አካባቢ ሸሽተው ሲሄዱም በመከታተል በህዝቡ ላይ ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፣ ከ150 በላይ ሰዎች ቆስለዋል። አንዳንድ ወጣቶች የፖሊሶችን መሳሪያዎችና ዱላቸውን ቀምተው በአንዳንድ ፖሊሶች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።
የካቲት 12 ቡናና አርባምንጭ ከነማ በተጫወቱበት ወቅት፣ ተነሱ የሚል ወረቀት የተበተነ ሲሆን፣ ያንን ተከትሎ የጸጥታ ቁጥጥሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ብሎ እንደነበር ታዛቢዎች ገልጸዋል። ፖሊሶች በከተማው ወጣቶች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዳቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።