የካቲት ፳፪ ( ሃያ ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜናዊ ሞዛምቢክ የአውራጃ አስተዳደር በህገ ወጥመንገድ ወደ ሞዛምቢክ ገብተዋል ያላቸውን 36 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ የአገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ። ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተደብ ቀው መያዛቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ዘካርያ ናኩቴ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። በእስር ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ እንደሚሞከርም አክለው ተናገረዋል።
ከተለያዩ አገራት የመጡ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች በሞዛምቢክ የሚኖሩ ሲሆን የአገሪቱ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አገራቸው የመመለስ ስራዎችን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ባለፈው ሳምንት ብቻ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሞዛምቢክ በመግባት መኖር የጀመሩ ቁጥራቸው 3 ሽህ 220 የውጭ አገር ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ከእነዚህ ስደተኞች ውስጥ 1 ሽህ 634 ያህሉ በሰሜናዊ ሞዛምቢክ ካቦ ዴልጋዶ ግዛት በሕገወጥ የማእድን ማውጣት ስራ ላይ መሰማራታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የውጭ አገር ስደተኞች ውስጥ 1 ሽህ 561 ታንዛኒያዊያን ዜጎች ሲሆኑ የተቀሩት 73 ደግሞ የጋምቢያ፣ የሴኔጋል፣ የታይላንድ እና የማሊ ዜጎች መሆናቸውን የካቦ ዴልጋዶ የፖሊስ አዛዥን አብዱል ቻጉሮን ጠቅሶ አፍሪካን ሪቪው ዘግቧል።